የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት ናንሲ ፔሎሲ፤ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንሚን ኔታንያሁ ከፍልስጤም ጋር “ፈጽሞ” ሰላም የማስፈን ሐሳብ የለውም ሲሉ ተናገሩ፡፡ ፔሎሲ የሚወክሉት ዴሞክራቲክ ፓርቲ እምነት ነው ያሉትን “ሁለት ሀገራት በመመሥረት” ጉዳይም ኔታንያሁ ምንም ፍላጎት የለውም ሲሉ ተችተዋል፡፡
ናንሲ ፔሎሲ ይህን የተናገሩት፤ በእንግሊዝ ለንደን ከተማ በሚገኘው ቫንተም ሐውስ በተሰኘ የፖሊሲ ጥናት ተቋም ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ የቀድሞዋ አፈ ጉባኤ፤ ኔታንያሁ ከፍልስጤም ጋር በሚደረገው የሰላም ስምምነት ሒደት አፍራሽ ሚና ሲጫወት መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
የናንሲ ፔሎሲ ሀገር አሜሪካ ፍልስጤም እና እስራኤል ሁለት ሀገራት መመሥረት አለባቸው በሚል ሲቀርብ የቆየውን ሐሳብ በባለሥልጣናት በኩል ስታስተጋባ ብትቆይም፤ ፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሙሉ አባል ለመሆን የምታቀርባቸውን ጥያቄዎች ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን በመጠቀም ውድቅ በማድረግ ትታወቃለች፡፡ ሐሳቡ በምክር ቤቱ ለመጨረሻ ጊዜ በቀረበበት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ለፍልስጤም ጥያቄ 12 ሀገራት ድጋፍ ቢሰጡም፤ ውሳኔው እንዲሻር ያደረገችው አሜሪካ ነበረች፡፡ በወቅቱ በድጋፍ ከቆሙት መካከል ፈረንሳይ፣ ጃፓን እና ኮሪያ ይኙበታል፡፡
በፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ “ሥነ-ምግባር የጎደለው ነው” በሚል ትችት የተሰነዘረበት ርምጃ፤ በአሜሪካ ባለሥልጣናት ማስተባበያ የተሰጠበት ነበር፡፡ ከርምጃው በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን የተናገሩት በተባበሩት መንግሥት የአሜሪካ ምክትል አምባሳደር ሮበርት ዉድ፤ “አሜሪካ አሁንም ቢሆንም ሁለት አገራት መመሥረት አለባቸው የሚለውን ሐሳብ ትደግፋለች”፤ ያሳለፉትን ውሳኔም “ፍልስጤም አገር መሆን አለባት የሚለውን ሐሳብ መቃወም አይደለም” ቢሉም፤ ድርድሩ “ከእስራኤል የሚደረግ መሆን አለበት” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ፍልስጤም እና እስራኤል ሁለት ሀገራት መመሥረት አለባቸው ሐሳብ መስተጋባት የጀመረው እ.አ.አ በ1990ዎቹ አንስቶ ነው፡፡ በዓለማችን 140 አገራት ፍልስጤምን እንደ ሀገር ዕውቅና ሰጥተዋታል፡፡ ከሀገራቱ ውስጥ በተለይ የዐረብ ሀገራት እና ድርጅቶች በቁጥር በርከት ብለው ይታያሉ፡፡ አሜሪካን ጨምሮ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና አውስትራሊያ እስካሁን ድረስ እውቅና አልሰጡም፡፡
የእስራኤል ወታደሮች ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በፍልስጤም ጋዛ ውስጥ በሰነዘሩት መጠነ ሠፊ ጥቃት፤ ቢያንስ 42 ሺሕ ንጹሐንን መግደላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












