Homeየቲቪ ፕሮግራሞችሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቁርኣን እና አዛን ውድድር ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተከናወነ

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቁርኣን እና አዛን ውድድር ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተከናወነ

በአዲስ አበባ ከተማ ለሚካሄደው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቁርኣን እና አዛን ውድድር ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በዛሬው እለት ተከናወነ። የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኩ በሁለት ዙር የሚከናወን መሆኑ በአዘጋጆቹ ተገልጿል።

ለቁርኣን እና አዛን ውድድሩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ዛሬ እሑድ ጥቅምት 3/2017 የተከናወነው በአዲስ አበባ ኤሊያና ሆቴል ነው። በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የቁርኣን ውድድሩ አዘጋጅ ዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርኣን ማኅበር ተወካዮች የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱ በሁለት ዙር የሚከናወን መሆኑን በመግለጽ፣ በቀጣይ ተመሳሳይ መርሐ ግብር እንደሚኖር ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የቁርኣን ውድድር ሊካሄድ መሆኑን አዘጋጆቹ ያስታወቁት መስከረም 21/2017 በሰጡት መግለጫ ነበር። በቁርኣን ውድድሩ ዐቢይ አስተባባሪዎች በኩል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከናወነው ዓለም አቀፍ የቁርኣን ውድድር፤ ከሁለት ወራት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ለማካሔድ እቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡

እንደ “ዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርኣን ማኅበር” መግለጫ ከሆነ፤ በዘንድሮው ዓለም አቀፍ ውድድር “በተወዳዳሪነት፣ በዳኝነት እና ለክብር እንግድነት በርካታ የውጭ እንግዶች” ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ በውድድሩ ላይ በመጀመርያው ዙር ከነበረው በቁጥር የላቁ የተሳታፊ ሀገራት እንደሚጠበቅ የገለጹት አስተባባሪዎቹ፤ ውድድሩ የውጪ መገናኛ ብዙኃንን ሽፋን ያገኛል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርኣን ማኅበር የቁርአንና የአዛን ውድድሩን ወጪ ለመሸፈን ያስችለኛል ያለውን የገቢ ማሰባሰቢያ ዛሬ ጥቅምት 3/2017 እንደሚያካሄድም ያስታወቀው በዚሁ መግለጫ ወቅት ነበር። በዛሬው እለት በተከናወነው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ግለሰቦች እና ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመርያው ዓለም አቀፍ የቁርኣን እና የአዛን ውድድር ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ስታዲየም መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ የዚሁ ተከታይ የሆነው ሁለተኛው ዙር ውድድር ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚካሔድ የተገለጸው ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ትክክለኛ ቀኑ እንዲሁም የዝግጅቱ ሥፍራ ይፋ አልተደረገም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular