የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል የሚያካሂደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ የፊታችን ሰኞ እንደሚጀመር አስታወቀ። ኮሚሽኑ በጅግጅጋ፣ ጎዴና ዶሌ አዶ ከተሞች የቅስቀሳ ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
የምክክር ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል የሚያካሂደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 4/2017 እንደሚጀመር ያስታወቀው በዛሬው እለት ነው።
የሶማሌ ክልል የምክክር መድረክ የሚከናወነው፣ ኮሚሽኑ የአፋር አጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው።
በአፋር አጀንዳ ማሰባሰብ መድረኩን የሚያካሄደው ኮሚሽኑ፤ በቀጣይ ጊዜያት በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና በኦሮሚያ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍን ለማከናወን ዝግጅቶችን እያከናወነ እንደሚገኝ ቀደም ብሎ ገልጾ ነበር። የኮሚሽኑ ኃላፊዎች በሰጧቸው መግለጫዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሐ ግብሩን እስከ ጥቅምት 30/2017 ለማጠናቀቅ እድቅ መያዛቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ውይይት እያካሄደ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታኅሣሥ 2014 በጸደቀ የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ በመንግሥት እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮችን እንደሚለይ አሥፍሯል።
ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡለትን እነዚህን አጀንዳዎች ካደራጀ በኋላ ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የመለየት ሚና በአዋጁ ተሰጥቶታል። (ሚንበር ቲቪ)












