በአሜሪካ ኖክስ ካውንቲ ፎቶግራፍ ለማንሳት በሚል በፖሊስ ሒጇቧን እንድታወልቅ የተገደደችው አሜሪካዊቷ ለይላ ሶሊዝ፤ በአካባቢው ፖሊስ መምሪያ ላይ ክስ የመሠረተችው በተያዘው ሳምንት ነው፡፡
ፖሊስ ለይላ ሶሊዝ ከፍቃዷ ውጪ ፎቶግራፍ ለማንሳት በሚል ሒጃቧን እንድታወልቅ ያስገደዳት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በቴኔስ ዩኒቨርሲቲ ፍልስጤምን በሚደግፍ ሠልፍ ላይ ተሳትፋ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ነው፡፡ አሜሪካዊቷ ባቀረበችው ክስ ፖሊስ ሃይማኖታዊ መብቷ ላይ ጥሰት እንደፈጸመ ገልጻለች፡፡
ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ የኖክስ ካውንቲ ፖሊስ መምሪያ በወቅቱ ለይላን በቁጥጥር ስር ካዋላት በኋላ ለሰዓታት በጣቢያው እንድትቆይ በማድረግ ለሰነድ ማስረጃ ለመያዝ በሚል ሒጃቧን በግዳጅ በማስወለቅ ፎቶግራፍ እንድትነሳ አድርጓል፡፡ ፖሊስ በፎቶግራፍ ካስቀራቸው ሁለት ፎቶግራፎች መካከል አንደኛው ያለ ሒጃብ የተነሳ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በሒጃብ መሆኑም በዘገባው ተመላክቷል፡፡
ፖሊስ ካስቀራቸው ሁለት ፎቶግራፎች ውስጥ ለይላ ሶሊዝ ያለ ሒጃብ የተነሳችውን ፎቶግራፍ ለመዝገብ ቤት አገልግሎት ብቻ ለማዋልና ለሦስተኛ አካል እንደማይጋራ የተነገራት ቢሆንም በመምሪያው ድረ ገጽ ላይ እንዲለጠፍ ተደርጓል፡፡ በዚህም የለይላ ሶሊዝ ፎቶግራፍ ያለ ፍቃዷ በመቶዎች ሰዎች እንዲታይ ሆኗል፡፡
ይህ የፖሊስ ድርጊት ያስቆጣት አሜሪካዊቷ በአካባቢው ፖሊስ ላይ ክስ መሥርታለች፡፡ የለይላ ጠበቃ ዳንኤል ሆርዊዝ ፖሊስ የጣሰው የፌዴራል እና የቴኔስን ግዛት ፖሊሲ መሆኑን በመጥቀስ፤ በጉዳዩ ላይ ክስ ማስያዛቸውን ጠቁሟል፡፡ ጠበቃዋ በክሱ ላይ ደንበኛው ለደረሰባት ጉዳት ፎቶግራፉ ከድረ ገጹ ላይ እንዲሰረዝ የጠየቀ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም የገንዘብ ካሣ እና በተመሣሣይ ጉዳዮች ላይ የፖሊሲ ለውጥ እንዲደረግ ሙግት ገጥሟል፡፡
በቴኔስ ግዛት ከዚህ ቀደም በተመሣሣይ ባለፈው ዓመት ሶፊያ ጆንስተን የተባለው ሙስሊም ሴት፤ ሒጃቧን እንድታወልቅ ያስገደዳት የረዘርፎርድ ካውንቲ ላይ ክስ በመመሥረት ካውንቲው የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግ ማስገደደድ ችላለች፡፡
ለይላ ሶሊዝ ክስ የመሠረተችበት የአሜሪካ ኖክስ ካውንቲ ፖሊስ መምሪያ እስካሁን ድረስ ስለ ጉዳዩ ያለው ነገር የለም፡፡ ሆኖም በሀገሪቱ ሙስሊም ሴቶች በተለይ በእስር ቤቶች የሚስተናገዱበት መንገድ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች እንዲሰነዘሩ አድርጓል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












