Homeዜናና ወቅታዊዜናየአል ነጃሺ መስጂድን ዕድሳት በስምንት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቀቅ እየተሠራ ነው ተባለ

የአል ነጃሺ መስጂድን ዕድሳት በስምንት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቀቅ እየተሠራ ነው ተባለ

በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የአል ነጃሺ መስጂድን ዕድሳት በስምንት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቀቅ እየተሠራ መሆኑ ተነገረ፡፡ የመስጂድ ዕድሳቱ በጦርነት ጉዳት ያስተናገደውን የመስጂዱን ውስጠኛ ክፍል እንዲሁም በዝናብ እና በሌሎች ሁኔታዎች የተጎዱ ሥፍራዎችን የሚያካትት መሆኑንም ባለሞያዎች ገልጸዋል፡፡

የአልነጃሺ መስጂድ ዕድሳት መስከረም 13/2017 መጀመሩን “ሚንበር ቲቪ” በመስጂዱ ዕድሳት ከሚሳተፉ ባለሞያዎች ሰምቷል፡፡ እንደ ባለሞያዎቹ ከሆነ የዕድሳት ሥራው የሚከናወነው በትግራይ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርገው በቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ፒካ) አማካኝነት ነው፡፡ ሥራው በዋነኝነት በሁለቱ አካላት ትብብር የሚከናወን ቢሆንም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እንዲሁም የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ተሳታፊ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

የግንባታውን ወጪ የሚሸፍነው የቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ቲካ)፤ በሀገሪቱ የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኝ የልማት መምሪያ ነው፡፡ ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም በተመሣሣይ የመስጂዱን ዕድሳት ለማከናወን እየሠራ በነበረበት ወቅት፤ በክልሉ ጦርነት በመከሰቱ ምክንያት ሥራውን ማቆሙ ተነግሯል፡፡ በ2013 በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት በመስጂዱ ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ ዕድሳቱን በድጋሚ ለማከናወን፤ ከአምስት ወራት በፊት ከትግራይ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ማድረጉ ታውቋል፡፡

መስጂዱ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ያስተናገደው በውስጠኛው ክፍል፣ በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች መቃብር እና በእልፍኙ ነበር፡፡ እየተከናወነ የሚገኘው የዕድሳት ሥራ እነዚህን ጨምሮ በዝናብ እና ሌሎች ሁኔታዎች የደረሰውን ጉዳት የሚያካትት መሆኑን “ሚንበር ቲቪ” ያናገራቸው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በዕድሳቱ እየተሳተፉ የሚገኙ ባለሞያ ተናግረዋል፡፡

የታሪካዊው አል ነጃሺ መስጅድ ጥገና ከዚህ ቀደም በግንቦት 2016 እንደሚጀመር በቱሪዝም ሚኒስቴር ኃላፈዎች ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፤ ከተጠቀሰው ጊዜ ለሦስት ወራት ዘግይቷል፡፡ ሚኒስቴሩ ዕድሳቱ የዘገየበትን ምክንያት እስካሁን ድረስ አልገለጸም፡፡ ሚኒስቴሩ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ፤ ለመስጅዱ “ደረጃውን የጠበቀ የጥገና ሥራ” ለማከናወን የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጾ ነበር፡፡

ዕድሳት የተጀመረለት አል ነጃሺ መስጅድ፤ ከትግራይ ክልል ዋና መቀመጫ መቐለ ከተማ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ታሪካዊውን መስጂድ በዩኒስኮ ለማስመዝገብ እየተሠራ መሆኑንም ከወራት በፊት የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የመቀለ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጥምረት ባዘጋጁት በመስጂድ መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ ኮንፍረንስ ላይ ተነግሯል፡፡ በ4 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው አል ነጃሺ መስጅድ፤ ዋናውን መስጂድ እንዲሁም ሁለት የቀብር ሥፍራዎችን በውስጡ ይዟል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular