አሜሪካ፤ እስራኤል በጋዛ እና በየመን ሐውሲዎች ላይ ለምትፈጽመው ጥቃት ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጓን አዲስ ሪፖርት አመለከተ፡፡ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የብራውን ዩኒቨርሲቲ ዋትሰን ኢንስቲትዩት፤ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በጋዛ ለተፈጸመው ጥቃት 17.9 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወታደራዊ ድጋፍ ሰጥታለች ብሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የጥናት ተቋም ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፤ አሜሪካ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ለእስራኤል የሰጠችው ወታደራዊ ድጋፍ፤ እስከዛሬ ድረስ ካደረገችው ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ የተጠቀሰው መጠን የገንዘብ ድጋፍ የጦር መሣሪያ ሽያጭን እንዲሁም ከሀገሪቱ የጦር መሣሪያ ክምችት ወደ እስራኤል እንዲተላለፍ ያደረገችውን የሚያጠቃልል መሆኑን ኢንስቲትዩቱ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከጦር መሣሪያዎቹ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ተተኳሾች እና 907 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ቦንቦች ናቸው፡፡
ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የብራውን ዩኒቨርሲቲ አጥኚዎች፤ መረጃ በማሰብሰብ ሒደት ውስጥ አሜሪካ ለእስራኤል ስለምትሰጠው የጦር መሣሪያ ድጋፍ የተሟላ መረጃ ለማግኘት አዳጋች ነበር ብለዋል፡፡ በዚህም በአንድ ዓመት በጋዛ ጭፍጨፋ የተመዘገበው 17.9 ቢሊዮን ዶላር የተሟላ መረጃ የያዘ አይደለም፡፡
ሀገሪቱ እስራኤል በጋዛ ለምትፈጽመው ጭፍጨፋ የምታደርገውን የጦር መሣሪያ ድጋፍ በተሟላ ሁኔታ ይፋ ባትመዘግብም፤ በአንጻሩ በዩክሬን ጦርነት የምትሰጠውን የጦር መሣሪያ ድጋፍ በተሟላ ሁኔታ በሰነድ አስቀምጣለች ተብሏል፡፡ እንደ አጥኚዎቹ ከሆነ በዚህ ሒደት ውስጥ የጆ ባደን አስተዳደር ለእስራኤል የሚሠጠውን የጦር መሣሪያ ድጋፍ መረጃዎችን ለመሸፋፈን ጥረት አድርጓል፡፡
በአንድ ዓመት ውስጥ ከ17 ቢሊዮን ዶላር በላይ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ያገኘችው እስራኤል፤ አሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ ከሚያገኙት መካከል ከፊት ረድፍ የምትሰለፍ ነች፡፡ ከአሜሪካ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ድጋፍ የሚያገኙ የእስራኤል ባለሥልጣናት በተለይ በጋዛ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ 42 ሺህ ገደማ ንጹሐንን ገድለዋል፡፡
አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠው ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሣሪያ ድጋፍ የንጹሐንን ሕይወት እየቀጠፈ በመቀጠሌ አሜሪካዊያንን ክፍፍል ውስጥ የከተተ መሆኑ ይነገራል፡፡ እስራኤል የምትሰነዝራቸው ጥቃቶች በርካታ የተፈናቃይ ጣቢያዎችንና ትምህርት ቤቶችን ማውደሙን በየእለቱ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












