በተያዘው ሳምንት በጅቡቲ የባሕር ዳርቻ በደረሰው የጀልባ መስጠም አደጋ የሞቱት በሙሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች መሆናቸው ተገለጸ፡፡ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 48 መሆኑን አስታውቋል፡፡
ኤምባሲው ይህን የገለጸው መስከረም 23/2017 ምሽት ባወጣው አጭር መግለጫው ነው፡፡ እንደ መግለጫው፤ መስከረም 21/2017 ማምሻውን ከየመን ወደ ጅቡቲ 320 መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰተኞች ይዘው የተነሱት ሁለት የስደተኞች ጀልባዎች በጅቡቲ ባህር ዳርቻ አከባቢ ሲደርሱ አደጋው ደርሷል፡፡
አደጋውን ተከትሎ 48 ፍልሰተኞች ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ 197 ፍልሰተኞች ደግሞ ከአደጋው ተርፈው ኦቦክ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የስደተኞች ካምፕ መድረሳቸውን ገልጿል፡፡ የተቀሩትን 75 ፍልሰተኞች አካል የማፈላለጉ ሥራ በነፍስ አድን ሠራተኞች መቀጠሉም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ በአደጋው ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን የገለጸው ኤምባሲው፤ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በየጊዜው እያደረሰ ያለውን ሞት ለመቀነስ ሁሉም ተቋማት በርብርብ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ኤምባሲው አክሎም ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማሳሰብ፤ በቀጣይ መንግሥት እነዚህ ግለሰቦች ላይ ጠንካራ ርምጃ የሚወስድ መሆኑን ገልጿል፡፡
በጅቡቲ የባሕር ዳርቻ አፍሪካዊያን ፍልሰተኞችን የጫኑ ጀልባዎች ሰጥመው ቢያንስ 45 ሰዎች መሞታቸውን ቀድሞ አስታውቆ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ኤጀንሲ (አይኦኤም) ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት እንዳወጣው መረጃ ከሆነ፤ 320 ሰዎችን አሳፍረው የነበሩት ጀልባዎች፤ በጅቡቲ ሰሜናዊ ምዕራብ ኮር አንጋር ክልል አቅራቢያ ከሚገኘው የባሕር ዳርቻ 150 ሜትር ወይም 492 ጫማ ሠጥመዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በተመሳሳይ ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 38 ሰዎችን የጫነ ጀልባ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ሲጓዝ በጅቡቲ የባሕር ዳርቻ ላይ በመስጠሙ የተሳፋሪዎች ሕይወት አልፏል። በሰኔ ወር እንዲሁ በዚሁ መንገድ ቢያንስ 49 ሰዎች ሞተዋል፡፡ በዚህ ጉዞ ከተሳፈሩት መካከል አብዛኛዎቹ ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሔዱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ነገር ግን ይህ የፍልሰተኞች ማቋረጫ በረድኤት ድርጅቶች እጅግ በጣም አደገኛ እና የተጨናነቀ ተብሎ የሚገለጽ ነው፡፡ “የምሥራቅ መንገድ” በሚል ሥያሜ የሚጠራው ይህ ማቋረጫ፤ የሕገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች በሥፋት የሚርመሰመሱበት አካባቢ መሆኑም ይነገራል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












