የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን፤ ለሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን በጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ መከላከያ መንገዶች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የሰጠው በዛሬ እለት ነው፡፡
ዛሬ ሐሙስ መስከረም 23/2017 በባለሥልጣኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተሠጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ እስላማዊ ጉዳዮችን ዋንኛ አጀንዳ አድርገው የሚሠሩ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ከተለያዩ ቤተ እምነቶች የተወከሉ የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ሥልጠናውን የከፈቱት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሐመድ ኢድሪስ፤ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የሚያሠራጯቸው ይዘቶች “በኢትዮጵያ ተከብሮ የቆየውን የሃይማኖት መቻቻልና አብሮነት ለማጠናከር እንዲሁም በሰላም እሴቶች ግንባታ ላይ ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችል” ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ግብረ ገብነትን በማስተማር ትውልድን ከማነፅ በተጨማሪ የጋራ እሴቶች እንዲጠናከሩ፣ አብሮነት እና ወንድማማችነት እንዲጎለብት የመሥራት ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ከጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ራሱን እና አካባቢውን እንዲጠብቅ ግንዛቤ ሊፈጥሩ የሚችሉ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን በአስተምሮታቸው የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል መፍትሄ በሚያመጣ፣ ሀገር በሚገነባና መልካም ዜጋን በሚያንፅ ጉዳይ ላይ በማተኮር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመቆጣጠር በ2011 አዋጅ ጸድቆ በሥራ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የማህበረሰብ ጠንቅ ነው የሚባላውን የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር የጣው አዋጅ፤ ስርጭቱንና መበራከቱን ለመቆጣጠር በሚል ኣላማ የወጣ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












