Homeዜናና ወቅታዊዜናሴቶችን ያሳትፋል የተባለ ዓለም አቀፍ የቁርኣን ውድድር በአዲስ አበባ ሊካሔድ ነው

ሴቶችን ያሳትፋል የተባለ ዓለም አቀፍ የቁርኣን ውድድር በአዲስ አበባ ሊካሔድ ነው

በኢትዮጵያ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቁርኣን እና የአዛን ውድድር በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሔድ መሆኑን አዘጋጆቹ ገለጹ፡፡ የውድድሩ አዘጋጅ “ዘይድ እብን ሳቢት የቁርኣን ማኅበር” በውድድሩ ለመጀመርያ ጊዜ በ30 ጁዝ የሴቶች የቁርኣን “ሒፍዝ” ውድድር እንደሚከናወን አስታውቋል፡፡

ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 21/2017 በቁርኣን ውድድሩ ዐቢይ አስተባባሪዎች በኩል በአዲስ አበባ ከተማ ኤልያና ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከናወነው ዓለም አቀፍ የቁርኣን ውድድር፤ ከሁለት ወራት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ለማካሔድ እቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡ አስተባባሪዎቹ ከሁለት ወራት በኋላ ውድድሩ እንደሚካሔድ ቢገልጹም፤ ትክክለኛ ቀኑን እንዲሁም የዝግጅቱን ሥፍራ ይፋ አላደረጉም፡፡

እንደ “ዘይድ እብን ሳቢት የቁርኣን ማኅበር” መግለጫ ከሆነ፤ በዘንድሮው ዓለም አቀፍ ውድድር “በተወዳዳሪነት፣ በዳኝነት እና ለክብር እንግድነት በርካታ የውጭ እንግዶች” ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ በውድድሩ ላይ በመጀመርያው ዙር ከነበረው በቁጥር የላቁ የተሳታፊ ሀገራት እንደሚጠበቅ የገለጹት አስተባባሪዎቹ፤ ውድድሩ ውጪ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን ያገኛል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በመግለጫው ላይ በቀደመው ውድድር ከነበሩት በተጨማሪ ይሳተፋሉ የተባሉ ሀገራት እንዲሁም ሽፋን ይሰጣሉ የተባሉ “ዓለም አቀፍ” ብዙኃን ሥም አልተጠቀሰም፡፡  

በዘንድሮ ዓመት በሚከናወነው ውድድር ሴቶች የሚሳተፉበት ዘርፍ እንደሚኖር የገለጹት አስተባባሪዎች፤ ይህም የውድድሩን አሳታፊነት እና ድምቀት የሚጨምር ነው ብለዋል፡፡ የውድድሩ አካል የሚሆነው የሴቶች ዘርፍ ውድድር “በሠላሳ ጁዝ ሒፍዝ” የሚደረግ መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ በሴቶች ዘርፍ ለሚካሄደው ውድድር እንደ ወንዶቹ ሁሉ ቀድሞ ማጣሪያ የሚደረግበት መሆኑን ከአስተባባሪዎቹ መካከል የሆኑት አስታዛ ፋጡማ ሐሰን ተናግረዋል፡፡

ዘይድ እብን ሳቢት የቁርኣን ማኅበር የቁርአንና የአዛን ውድድሩን ወጪ ለመሸፈን ያስችለኛል ያለውን የገቢ ማሰባሰቢያ ጥቅምት 3/2017 እንደሚያካሄድ በዚሁ መግለጫ ላይ ያነሳው ጉዳይ ነው፡፡ ለዓለም አቀፉ የቁርኣን ውድድር መሳተፍ የሚችሉ ተወዳዳሪዎችንን ለመለየትና በየክልል ከተሞች የቁርኣን ውድድሮችን “በደመቀ ሁኔታ ለማካሄድ ታቅዶ” ዝግጅት መጀመሩም ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመርያው ዓለም አቀፍ የቁርኣን እና የአዛን ውድድር ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ስታዲየም መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular