መንግሥታዊ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ፡፡ ባንኩ የተጨማሪ እሴት ታክስ ታሪፍ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው ከዛሬ ማክሰኞ አንስቶ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ባንኩ ከመስከረም 21/2017 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የተጨማሪ እሴት ታክስ፤ በሁሉም ምርት እና የአገልግሎት ዓይነቶች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ገልጿል፡፡
በሚከፈለው የምርት እና አገልግሎት ክፍያ ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ታሪፍ እንደተጨመረ ቢገልጽም፤ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ግን ባንኩ ማብራሪያ አልሰጠም፡፡ በአንጻሩ የተጨማሪ እሴት ታክስ ታሪፍ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገበትን መነሻ የገለጸ ሲሆን፣ በቅርቡ የወጣው አዲስ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር አዋጅ በቁጥር 1341/2016 ባወጣው መሠረት፤ ባንኮች በሚሰጧቸው አገልግሎቶች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲጣል ታውጇል፡፡ ከሰኔ 27/2016 ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ላይ ሙሉ በሙሉ በፌዴራል በጀት የሚተዳደሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተካተቱበት ነው፡፡ መንግሥታዊው ባንክም ይህን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ የተጨማሪ እሴት ታክስ ታሪፍ እንደተጨመረ ነው ያስታወቀው።
መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት በግብር 1.15 ትሪሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም ሌሎች የመንግሥታዊ ተቋማት በሚሰጧቸው አገልግሎት ላይ የታሪፍ ማሻሻያ አድርገዋል፡፡ ማሻሻያ ካደረጉት መካከል ኢትዮ ቴሌኮም የታሪፍ ማሻሻያውን እንደ ንግድ ባንክ ሁሉ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












