Homeዜናና ወቅታዊዜናበአሜሪካ ምርጫ ሙስሊሞች ካማላ ሐሪስን ከመምረጥ እንዲቆጠቡ ዕውቅ የእስልምና መምሕራን እና ኢማሞች...

በአሜሪካ ምርጫ ሙስሊሞች ካማላ ሐሪስን ከመምረጥ እንዲቆጠቡ ዕውቅ የእስልምና መምሕራን እና ኢማሞች ጥሪ አቀረቡ

በኅዳር ወር መገባደጃ በሚከናወነው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ሙስሊሞች ካማላ ሐሪስን ከመምረጥ እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀረቡት አምስት የእስልምና መምሕራን እና ኢማሞች ናቸው፡፡ መራጮች ከካማላ ሐሪስ ይልቅ ሦስተኛውን ፓርቲ እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከፍተኛ ትንቅንቅ በሚያስተናግደው የአሜሪካ ምርጫ ሙስሊም የሀገሪቱ ዜጎች ከዴሞክራቲክ እጩዋ ካማላ ሐሪስ ይልቅ በሦስተኛ አማራጭነት የቀረበውን ፓርቲ እንዲመርጡ ጥሪ ያቀረቡት ዶክተር ያሲር ቃዲ፣ ኢማም ዑመር ሱለይማን፣ ዳውድ ወሊድ፣ ዶክተር ሻዲ ኤልማስሪ እና ኢማም ቶመ ፋቺን ናቸው፡፡

መምሕራኑ እና ኢማሞቹ በፈረሙበት ደብዳቤ ላይ፤ ሙስሊም መራጮች ዴሞክራቲክ ፓርቲን አትምረጡ ለማለታቸው በሥልጣን ላይ የሚገኘው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ካማላ ሐሪስ አስተዳደር በጋዛ ጉዳይ የያዘውን አቋም አንስተዋል፡፡ ሚድል ኢስት ዐይ ተመልክቼዋለሁ ባለው ደብዳቤ፤ መምሕራኑ እና ኢማሞቹ “የወደፊቱን ማወቅ ባንችልም፤ አሁን ግን በጋዛ የወንድም እና እህቶቻችንን ደም ያፈሰሰውን አስተዳደር በመደገፍ እጃችንን አናረክስም” ማለታቸውንም አስፍሯል፡፡

እንደ ዘገባው ከሆነ መምሕራኑ እና ኢማሞቹ አሜሪካዊያን ሙስሊሞች ዴሞክራቶችን ከመምረጥ ይልቅ ድምጻቸውን እንዲሰጡ የጠየቁት በጂል ስቴይን ለሚመራው ግሪን ፓርቲ ነው፡፡ የአረንጓዴ ፖለቲካ የሚያራምደው ፓርቲው፤ በተለይ በአካባቢ ጥበቃ፣ አመፅን በመጠየፍ፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ በመቆም እንዲሁም በፀረ ጦርነት አቋሙ ራሱን የሚያስተዋውቅ ነው፡፡

“ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ” ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይፋ ባደረገው የሕዝብ አስተያየት፤ የእስልምና ባሕል በሥፋት ይንጸባረቅበታል በሚባለው የሚቺጋን ግዛት 40 በመቶ ሙስሊም መራጮች ለጂል ስቴይን ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ግዛት ካማላ ሐሪስ 12 በመቶ ብቻ ድምጽ ሲያስመዘግቡ፤ የሪፐብሊካን እጩው ዶናልድ ትራምፕ 18 በመቶ አግኝተዋል፡፡ የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ስቴይን ፀረ እስራኤል አቋም በማራመድ የሚታወቁ ናቸው፡፡ ሆኖም የሚመሩት ፓርቲ በአሜሪካ ምርጫ ፉክክር ተጽዕኖው እምብዛም መሆኑ ይነገራል፡፡

ምርጫውን በተመለከተ የእስልምና መምሕራኑ ዶክተር ያሲር ቃዲ እና ኢማም ዑመር ሱለይማንን ጨምሮ በፈረሙት ደብዳቤ፤ አሜሪካዊያን ሙስሊሞች የሚፈልጉትን ዕጩ ባያገኙም በፍጹም ከምርጫው እንዳይቀሩ አያይዘው ማስታወሻ አስፍረዋል፡፡

አሜሪካ የምትደግፋት እስራኤል ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በጋዛ ቢያንስ 41 ሺሕ ንጹሐንን መግደሏን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡ ከሟቾቹ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘት ሕጻናት እና እናቶች ናቸው፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular