የእስራኤል ባለሥልጣናት በጋዛ እና ሊባኖስ የምትፈጽመውን ጥቃት የሚቃወሙ ሠልፎች በስዊድን ስቶክሆልም፣ በፈረንሳይ ፓሪስ እንዲሁም በፊንላንድ ሔልሲንኪ ከተሞች ተካሔደ፡፡ ሠልፈኞቹ “ነጻ ፍልስጤም” እና “እጃችሁን ከሊባኖስ ላይ አንሱ” የሚሉ መፈክሮችን ሰያስተጋቡ ታይተዋል፡፡
በስዊድን የተቃውሞ ሠልፍ የተካሔደው እስራኤል የሒዝቡላህ መሪ የነበሩት ሐሰን ነስረላህን መግደሏን ካሳወቀች በኋላ ነው፡፡ በምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን በመካከለኛው መሥራቅ “ተጽዕኗቸው የጎላ ነው” በሚል ይወደሱ የነበሩት ሐሰን ነስረላህ፤ የመገደላቸው ዜና በድርጅታቸው ይፋ የተደረገው ከሁለት ቀን በፊት መስከረም 18/2017 ነው፡፡

በጋዛ የሚፈጸመውን ጥቃት ሲቃወሙ የቆዩትን የነስረላህን ግድያ ተከትሎ፤ ያለፉትን ሳምንታት በውጥረት ውስጥ በቆየው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ግጭት መባባሱን የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ላይ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በስዊድን ስቶክሆልም ከተማ ወደሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ያመሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠልፈኞች ባደረጉት የተቃውሞ ትዕይንተ ሕዝብ፤ የፍልስጤምን እንዲሁም የሊባኖስን ሰንደቅ አላማ ይዘው ታይተዋል፡፡ በዚሁ የተቃውሞ መርሐ ግብር ላይ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው መጠነ ሰፊ ጥቃት እንዲቆም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያሳድር የሚጠይቁ ድምጾች ተስተጋብተዋል፡፡
አልጀዚራ አናገርኳቸው ካላቸው ሠልፈኞች መካከል የሆነው ኢትዮጵያዊ የዘር ሐረግ ያለው ስዊናዊው አርቲስት እና አክቲቪስት ሳሙኤል ግርማ፤ እስራኤልን “አሸባሪ” ሀገር ሲል የገለጸ ሲሆን፣ ከእስራኤል ጋር የሚደረግ የንግድ ልውውጥ እንዲቆም ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የተቃውሞ ሠልፎቹ በተመሳሳይ በፈረንሳዩዋ ፓሪስ ከተማ እንዲሁም በፊንላንድ ሔልሲንኪ ከተሞች ተካሔደዋል፡፡ በፓሪስ ኢኖሰንትስ ፋውንቴን አቅራቢያ በተካሔደው ሠልፍ ላይ “የጋዛ ጭፍጨፋ ይቁም” እንዲሁም “ቦይኮት እስራኤል” የሚሉ መፈክሮችን የያዙ የከተማዋ ሠዎች ታይተዋል፡፡ በተጨማሪም የፍልስጤም መገለጫ የሆነ የአንገት ሻርፕ እና ከሁለት ዓመት በፊት በእስራኤል ወታደሮች የተገደለችውን የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ሺረን አቡ አቅሌህን ፎቶግራፍ የያዙ የፍልስጤም ደጋፊዎች በአደባባይ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡
በሦስቱ ከተሞች ከተካሔዱት የተደራጁ የተቃውሞ ሠልፎች ውጪ በቱርኪዬ ኢስታምቡል ከተማ በባቡር ጣቢያ አቅራቢያ እስኤልን የሚያወግዙ ድምጾች ተሰምተዋል፡፡ ፍልስጤምን የሚወክሉ ምልክቶችን ያነገቡ ተቃውሞ አድራጊዎች፤ የእስራኤል ባለሥልጣናት ተጠያቂ እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሕንዷ ካሽሚር ከተማም እንዲሁም የሂዝቡላህ መሪ ሐሰን ነስሩላህ መገደላቸውን በመቃወም ሠልፍ አስተናግዳለች፡፡ ሠልፈኞቹ ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር የምትደርገውን የጦር መሣሪያ ስምምነት እንድታቋርጥ ጠይቀዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተገናኘ የሐሰን ነስሩላህ ግድያ በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኘው ዴርአልባላህ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማዊያንን ሐዘን ውስጥ የጣለ መሆኑን የአልጀዚራ ዘጋቢዋ ማራም ሑመድ ከሥፍራው ያናገረቻቸውን ተፈናቃዮች ዋቢ አድርጋ ዘግባለች፡፡ ለጋዜጠኛዋ ቃሏን የሰጡት የ74 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ፍልስጤማዊቷ በስማ አል ሄሉ፤ የሐሰን ነስረላህን ግድያ የሰሙት ከባለቤታቸው ጋር ቁርስ ለመመገብ በተሰናዱበት ወቅት እንደነበር በማስታወስ፤ ክፉኛ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ ነስረላህ እድሜያቸውን በሙሉ ከጋዛ ጎን በጽናት መቆማቸውን በማስታወስ፤ እስራኤልን በጽኑ በመቃወም በመገናኛ ብዙኃን የሚያሰሟቸው ንግግሮችም “ብርታት ይሆነኝ ነበር” ብለዋል፡፡
ሐሰን ነስረላህ የተገደሉባት ሊባኖስ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን አውጃለች፡፡ በሀገሪቱ ባለአደራ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ ሚቃቲ ይፋ የተደረገው ይህ ብሔራዊ ሐዘን ዛሬ ሰኖ የሚጀምር ነው፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












