Homeዜናና ወቅታዊዜናበአፋር ክልል በቀጣይ ሳምንት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ እንደሚጀመር ኮሚሽኑ አስታወቀ

በአፋር ክልል በቀጣይ ሳምንት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ እንደሚጀመር ኮሚሽኑ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል በቀጣይ ሳምንት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ እንደሚጀመር አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ በሒደቱ በክልሉ ከሚገኙ 49 ወረዳዎች የተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት ተወካዮች እንደሚሳተፉ ገልጿል፡፡

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል የሚከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ መስከረም 21/2017 እንደሚጀመር ያስታወቀው በዛሬ እለት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ የተጀመረው የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ እስካሁን ድረስ በ5 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳድሮች ሲከናወን ቆይቷል ያለው ኮሚሽኑ፤ የአፋር ክልል ተረኛው የአጀንዳ ማሳባሰብ መድረክ የሚከናወንበት ክልል መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በአፋር በሚከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ በክልሉ ከሚገኙ 49 ወረዳዎች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍል ወኪሎች፣ በክልሉ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ማኅበራት ወኪሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከክልሉ የመንግሥት አካላት የተወከሉ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ እና በሐረሪ ክልሎች ኮሚሽኑ አጀንዳ ማሰባሰቡ የሚታወቅ ነው፡፡

ኮሚሽኑ በቀጣይ ጊዜያት በሶማሌ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና በኦሮሚያ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍን ለማከናወን ዝግጅቶችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ የኮሚሽኑ ኃላፊዎች በሰጧቸው መግለጫዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሐ ግብሩን እስከ ጥቅምት 30/2017 ለማጠናቀቅ እድቅ መያዛቸውን ገልጸው ነበር፡፡

በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ውይይት ለማካሄድ በሒደት ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታኅሣሥ 2014 በጸደቀ የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ በመንግሥት እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮችን እንደሚለይ አሥፍሯል። ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡለትን እነዚህን አጀንዳዎች ካደራጀ በኋላ ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የመለየት ሚና በአዋጁ ተሰጥቶታል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular