Homeዜናና ወቅታዊዜናየዓለም አቀፍ የ“ሰረብራል ፓልሲ” ጉዳተኞች ቀንን አስመልክቶ የተዘጋጀው የእግር ጉዞ መራዘሙን አዘጋጆቹ...

የዓለም አቀፍ የ“ሰረብራል ፓልሲ” ጉዳተኞች ቀንን አስመልክቶ የተዘጋጀው የእግር ጉዞ መራዘሙን አዘጋጆቹ ገለጹ

እዝነት አካል ጉዳተኛ ሕፃናት እና ወላጆች መርጃ ድርጅት በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የ“ሲፒ” ወይም “ሰረብራል ፓልሲ” ጉዳተኞችን ቀን አስመልክቶ ሊያደርግ የነበረውን የእግር ጉዞ ማራዘሙን አስታወቀ፡፡ ለተሳታፊዎች ቲሸርት መዘጋጀቱን የገለጹት የድርጅቱ ኃላፊዎች፤ ኅብረተሰቡ ጥቅምት 3/2017 በሚከናወን የእግር ጉዞ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ድርጅቱ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ረቡዕ መስከረም 15/2017 በቅጽር ግቢው በሰጠው መግለጫ ነው፡፡ መስረም 26/ 2017 ሊካሄድ የነበረውን የእግር ጉዞ ለማራዘም የተገደደው በቀጣይ ቀናት በሀገሪቱ ከሚከበሩ ባሕላዊ እንዲሁም ሓይማኖታዊ በዓላት ጋር በተገናኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህም የእግር ጉዞውን ቀድሞ ከተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ በአንድ ሳምንት በማራዘም ጥቅምት 3/2017 ለማድረግ እቅድ ተይዟል፡፡

የድርጅቱ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ዘቢባ አሕመድ በመግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የቀን ለውጥ ማድረግ ያስፈለገው የሕዝቡን ትኩረት እና ድጋፍ በይበልጥ ለማግኘት እንዲሁም በዕቅዱ መሠረት ተደራሽነቱን ከፍ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የዓለም የሰረብራል ፓልሲ ጉዳተኞች ቀንን ተንተርሶ በአዲስ አበባ ከተማ የሚዘጋጀው መርሐ ግብር ሲከናወን፤ መነሻውን አድዋ 00፣ መዳረሻውን ኩባ ፓርክ በሚያደርግ የእግር ጉዞ ላይ ስለ ሲፒ ጉዳትና ሕፃናቱ በሚታገዙበት ሁኔታ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን ይሠራሉ ሲል ድርጅቱ ገልጿል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግሥት አካላት፣ አጋር ድርጅቶች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ከ5 ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ተጠብቋል፡፡ እዝነት አካል ጉዳተኛ ሕፃናት እና ወላጆች መርጃ ድርጅት ለእግር ጉዞው ቲሸርት ማዘጋጀቱንም በማስታወቅ ኅብረተሰቡ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡

“ሰረብራል ፓልሲ” የሚከሰተው ሚዛንን የሚጠብቀው እንዲሁም እንቅስቃሴን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል የተዛባ እድገት አልያም ጉዳት ሲኖረው መሆኑን የሕክምና ባለሞያዎች ይገልጻሉ፡፡ በ“ሴሬብራል ፓልሲ” የተጎዱ ሕጻናት መቆም፣ መቀመጥ እና መራመድ ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ 17 ሚሊዮን ሰዎች ከ“ሰረብራል ፓልሲ” ጋር እንደሚኖሩም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ “ሰረብራል ፓልሲ” በተመለከተ ግንዛቤ ማስጨበጫ በየዓመቱ የሚከበረው መስከረም 26 ወይም እ.አ.አ ጥቅምት 6 ነው፡፡

በሕመሙ ዙርያ ግንዛቤ ለመፍጠር የእግር ጉዞ ያዘጋጀው እዝነት አካል ጉዳተኛ ሕፃናት እና ወላጆች መርጃ ድርጅት፤ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ላለባቸው ሕፃናት የእንክብካቤ ማእከል የከፈተው በ2013 ነበር፡፡ ድርጅቱ ሃምሳ ለሚሆኑ ህፃናት የቴራፒ ህክምና አገልግሎት፣ የምግብ ምገባና የፅዳት አገልግሎት እንደሚሰጥ ያስታወቀ ሲሆን፣ ለሃያ የሕፃናቱ ችግረኛ ወላጆችም በድርጅቱ ውስጥ ተቀጥረው እንዲሠሩና የተለያዩ የሥራ ክሕሎት ስልጠናዎች በማሠልጠን፣ በማደራጀትና ሥራ ሠርተው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን እንዲደጉሙ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊዎቹ ይናገራሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular