Homeዜናና ወቅታዊዜናለፍልስጤም ዕውቅና ያልሰጡ ሀገሮች ውሳኔ እንዲያሳልፉ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ጥሪ አቀረቡ

ለፍልስጤም ዕውቅና ያልሰጡ ሀገሮች ውሳኔ እንዲያሳልፉ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ጥሪ አቀረቡ

የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ሬሲብ ጠይብ ኤርዶጋን፤ ለፍልስጤም ዕውቅና ያልሰጡ የዓለም ሀገሮች ውሳኔ በማሳለፍ የሀገርነት ዕውቅና በመስጠት እንዲቀላቀሏቸው ጥሪ አቀረቡ፡፡ ኤርዶጋን ከሒትለር ጋር ላነጻጸሩት የእስራኤሉ ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ የሰው ልጆች በቃህ ሊሉት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ጥሪውን ያቀረቡት በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው 79ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ ኤርዶጋን “እስካሁን የሀገርነት መሆን እውቅና ያልሰጡ ሀገራት በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከፍልስጤም ጎን እንዲቆሙ ግብዣ አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡ ለፍልስጤም የሀገርነት ዕውቅና የመስጠት ውሳኔ ከዚህ በላይ መዘግየት እንደሌለበትም አጽንኦት የሰጡበት ጉዳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ ንግግር ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋዛውን ጭፍጨፋ ለማስቆም አለመቻሉን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የድርጅቱ ውሳኔ የማሳለፍ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መሄዱንም በማንሳት ትችት ሰንዝረዋል፡፡ አያይዘውም እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጭፍጨፋ ያወገዙ ሲሆን፣ በእስራኤል ጥቃት ጋዛ ከተማ የሕጻናት እና እናቶች ትልቁ መቀበሪያ ሥፍራ መሆኑንም በመጥቀስ አሁንም ትኩረት እንዲደረግ ወትውተዋል፡፡ በጋዛ በሚፈጸመው ጥቃት እየሞቱ የሚገኙት ሕጻናት ብቻ ሳይሆኑ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሠራር ሥርዐት ጭምር ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በኤርዶጋን ንግግር ላይ ሌላው የተጠቀሰው ጉዳይ፤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀን እሑድ በእስራኤል ወታደሮች ተጥሶ እንዲዘጋ የተደረገው የአልጀዚራ ቴሌቪዥን የራማላህ ቢሮ ነው፡፡ ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ጥያቄ አለኝ ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ “በቀጥታ ሥርጭት የተገደሉት እንዲሁም በእስራኤል ወረራ ቢሮ ተጥሶ የተገባባቸው ጋዜጠኞች ባልደረቦቻችሁ አይደሉም ወይ?” ሲሉ ሞጋች ሐሳብ ሠንዝረዋል፡፡  

በአሁኑ ሰዓት ግጭቶችን ወደ ቀጣናው ሀገራት ጭምር በማዛመት የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ተጠያቂ በማድረግ፤ የሰውዬውን ድርጊት ለማስቆም መላው ዓለም በትብብር መቆም እንደሚኖርበትም አስታውሰዋል፡፡ ሒትለር ከ70 ዓመታት በፊት በሰው ልጆች ጥምረት እንደተገታው ሁሉ፣ ኔታንያሁ እና ገዳይ ኔትወርኩም በሰው ልጆች ጥምረት መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል፡፡

እስራኤል አንድ ዓመት ገደማ ባስቆጠረው በጋዛ በምትፈጽመው ጥቃት የተገደሉ ንጹሐን ቁጥር ከ40 ሺሕ ተሻግሯል፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular