Homeዜናና ወቅታዊዜናባለሥልጣኑ የመንገድ ርቀት በማይጠብቁ ግንባታዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር “ለድርድር የማይቀርብ” ነው አለ

ባለሥልጣኑ የመንገድ ርቀት በማይጠብቁ ግንባታዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር “ለድርድር የማይቀርብ” ነው አለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን የመንገድ ርቀት በማይጠብቁ ግንባታዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ለድርድር የማይቀርብ ነው ብሏል፡፡ “ሥነ ምግባር የጎደላቸው” ናቸው ያላቸው አመራሮችን እና ባለሞያዎችን ለሕገ ወጥ ግንባታ “ሽፋን በመስጠት” ውንጀላ አቅርቧል፡፡

ባለሥልጣኑ የመንገድ ርቀት በማይጠብቁ ግንባታዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ለድርድር የማይቀርብ ነው ያለው፤ ለከተማዋ ክፍለ ከተሞች ግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ፍቃድ ዳይሬክተሬት በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡ ምክትል ዳይሬክተር ዳዊት ሑንዴሳ በተጻፈው በዚህ ደብዳቤ ላይ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል ሕንጻዎች ከመንገድ መራቅ የሚኖርባቸው ርቀት (ሴትባክ)፣ የመሬት ሥፋት ዝቅተኛው ገደብ እንዲሁም የጎን ሥፋት (ፍሮንቴጅ) እንደሚገኝበት አስታውሷል፡፡

ውሳኔው ተግባራዊ እንዲደረግ ከዚህ ቀደም መመርያ ወርዷል ያለው ባለሥልጣኑ፤ ሆኖም አንዳንድ አልሚዎች “አስፈላጊውን” የዲዛይን ማሻሻያ ሳያደርጉ እና የግንባታ ማስጀመሪያ የእርከን ማሳወቂያ ሳይወስዱ የወጣውን ሕግ በመጣስ ከሕጉ ለማምለጥ ወደ ግንባታ ለመግባት ጥረት እያደረጉ እንዲገኙም ገልጿል፡፡ ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ “ሥነ ምግባር የጎደላቸው” ናቸው ያላቸው አመራሮችንና ባለሞያዎችን ሽፋን እየሰጡ ነው በሚል ጥቆማ እየመጣ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ ከዚህ በኋላ ለሚደረገው ግንባታ በማዕከል፣ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ደረጃ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ትእዛዝ አስተላልፏል፡፡

ባለሥልጣኑ በምንም መልኩ ለድርድር አይቀርቡም ያላቸው ደንቦች እንዲጠበቁ ያሳሰበ ሲሆን፣ ይህን ሕግ በመጣስ ግንባታ የሚያከናወኑ፣ በክፍለ ከተማቸውና በወረዳቸው “የግንባታ ሥራን በአግባቡ የማይከታተሉና የማይቆጣጠሩ፣ ሕገ ወጦችን ዐይቶ እንዳላየ በማለፍ ሽፋን በሚሰጡ” ላይ “የማያዳግም ርምጃ” እንደሚወስድ በደብዳቤው ላይ አስፍሯል፡፡

በከተማው ለሁሉም ክፍለ ከተሞች በተላለፈው መመርያ መሠረት ከ15 ሜትር እና በላይ ሥፋት ያላቸው መንገዶች የሚያዋስኗቸው ይዞታዎች ዝቅተኛው የቦታ ሥፋት ሴት ባክ ከተቀነሰ በኋላ ቢያንስ 500 ሜትር ካሬ መሆን እንደሞኖርበት ተደንግጓል፡፡ ይህ ካልተሟላ የግንባታ ፍቃድ አይሰጥም፡፡ በተመሳሳይ በእነዚህ መንገዶች ላይ ዝቅተኛው የሕንጻ የጎን ሥፋት ከ20 ሜትር ያላነሰ መሆን እንደሞኖርበት ተቀምጧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular