የአልጀዚራ የራማላህ ቢሮ በእስራኤል ወታደሮች ከበባ ውስጥ ገብቶ እንዲዘጋ ውሳኔ እንደተላለፈበት ጣቢያው ያስታወቀው ዛሬ እሑድ ማለዳ ነው። ወታደሮቹ ጣቢያው ወደሚገኝበት ሕንጻ በኃይል በመግባት በ45 ቀናት ዘግተው እንዲወጡ ለኃላፊዎች መመሪያ አስተላልፈዋል ተብሏል።
የእስራኤል ወታደሮች በኃይል በሠፈሩበት የፍልስጤሟ ራማላህ ከተማ የሚገኘውን በአልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ ስር የሚተዳደረውን የአልጀዚራ ቲቪን ቢሮ እንዲዘጋ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ የጠቀሱት ምክንያት አለመኖሩን የቢሮው ኃላፊ ዋሊድ አል ኦማሪ ገልጸዋል። ቢሮውን እንዲዘጋ በወታደሮች ትዕዛዝ የተሰጠው አልጀዚራ፣ እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ ዘገባ እንዳያስተላልፍ እግድ ተጥሎበት ነበር። ይህ ውሳኔ የመጣው ከቀዳሚው ውሳኔ አንድ ወር በኋላ ነው።

የሠፋሪዎቹን ወታደሮች ውሳኔ ተከትሎ በርካታ ዘገባዎችን ከዌስት ባንክ ለዓለም በማድረስ የምትታወቀው ኒዲ ኢብራሂም፣ ወታደሮቹ ሲሰነዝሩት ከነበረው ማስፈራሪያ አንጻር ቢሮው ይዘጋ መባሉ የሚያስደንቅ አይደለም ብላለች።
የጣቢያው የራማላህ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው የጋዜጠኞች እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ውሳኔውን እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርበዋል። ጋዜጠኞችን ኢላማ ያደረጉ ውሳኔዎች እውነት ተደብቆ እንዲቀር የሚያደርግ መሆኑንም ኦማሪ ተናግረዋል።
እስራኤል ከባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር አንስቶ በጋዛ ዳግም ጥቃት መሰንዘር ከጀመረች በኋላ 173 ጋዜጠኞችን መግደሏን ይፋዊ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ከእነዚህ መካከል የአልጀዚራ ጋዜጠኞቹ እስማኢል አልጉል እና ሰሚር አቡደቃ ይገኙበታል። የጣቢያው የዐረቢኛ ዘጋቢ እስማኢል አቡ አማርም በፅኑ ቆስሎ የአካል ጉዳት አስተናግዷል።












