የሩስያዋ ሞስኮ ከተማ 20ኛውን “ሙስሊም ኢንተርናሽናል ፎረም” ከትናንት ጁመዓ መስከረም 10/2017 አንስቶ ማከናወን ጀምራለች።
በነገው እለት የሚጠናቀቀው ፎረም፣ የተለያየ የእስልምና መሪዎች እና የሀገራት ባለሥልጣናትን ያሳተፈ ነው። ከሩሲያ ፌዴሬሽን ሙስሊሞች መንፈሣዊ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጋር ባንድነት የሚዘጋጀው መድረክ የዘንድሮ መሪ ቃል “የሰላም መንገድ፡ ውይይት በአብሮነት የመኖር መሠረት ነው” የሚል ነው።
በዚሁ ፎረም የሩሲያ ፌዴሬሽን ሙስሊሞች መንፈሣዊ አስተዳደር 30ኛ ዓመት እንዲሁም የሊቀመንበሩ ሙፍቲ ሸይኽ ራቪል ጋይኑትዲ 40ኛ ዓመት የአገልግሎት ዘመን እየተከበረ እንደሚገኙ የሀገሪቱ መገናኛ ብዘኃን ዘገባ ያመለክታል።
በፎረሙ ላይ ኢትዮጵያ የተሳተፈች ሲሆን፣ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም መገኘታው ታውቋል።
ሙስሊም ኢንተርናሽናል ፎረም ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር 19ኛ መድረኩን ሲያከናውን የተሳታፊዎች ትኩረት የነበረው የጋዛ ጉዳይ ነበር። በዘንድሮው ፎረም በተመሳሳይ የጋዛ የንጹሐን ሰቆቃ ይነሳል ተብሎ ተጠብቋል። (ሚንበር ቲቪ)












