የሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ ሚኒስቴር የዑምራ ሥነ ሥርዐት ለመከወን ወደ ቅዱሳን ከተሞች የሚያመሩ ምዕመናን አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ አሳሰበ። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምዕመናን አካላዊ ርቀት መጠበቃቸው ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚያግዝ አስታውቋል።
የሀገሪቱ ሐጅ ሚኒስቴር ይህን ያስታወቀው በኤክስ ገጹ ላይ ባሠፈረው ማስታወሻ ነው። ለሥነ ሥርዐቱ ወደ መካ እና መዲና ከተሞች የሚያመሩ ምዕመናን በዑምራ ሥነ ሥርዐት ክንውን ወቅት ጭንብል እንዲያጠልቁ በተደጋጋሚ ሲያሳውቅም ቆይቷል።
የሐጅ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት የክረምት ወራት መጀመሪያ የተጠናቀቀውን የሐጅ ክንውን ተከትሎ በመላው ዓለም ለሚገኙ ምዕመናን የዑምራ ቪዛ እየሰጠ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ባለፈው ዓመት በወጣው መረጃ መሠረት 13.5 ገደማ ምዕመናን የዑምራ ክንውን ፈጽመዋል። የሀገሪቱ መንግሥት በቀጣይ ዓመት ቁጥሩን በማሳደግ 15 ሚሊዮን ምዕመናንን ለመቀበል እቅድ መያዙን ገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት ለዑምራ ለሚደረግ ጉዞ ቀድሞ ለ30 ቀናት ይሰጥ የነበረው ቪዛ፣ ወደ 90 ቀናት መራዘሙም ይታወቃል። በአየር፣ በየብስ እና በባሕር ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚገቡ ምዕመናን፣ በፈለጉት አየር መንገድ እንዲመለሱም ፍቃድ ይሰጣቸዋል። ሴት የዑምራ ተጓዦችም ቀድሞ ከነበረው አሠራር በተለየ በተናጠል መጓዝ ተፈቅዶላቸዋል።












