Homeዜናና ወቅታዊዜናአውስትራሊያ ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለማቀብ ያስችላል ያለችውን አዲስ አሠራር ልትዘረጋ ነው

አውስትራሊያ ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለማቀብ ያስችላል ያለችውን አዲስ አሠራር ልትዘረጋ ነው

አውስትራሊያ ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለማቀብ ያስችላል ያለችውን የዕድሜ ማረጋገጫ የመጠየቅ አሠራር ልትዘረጋ መሆኑን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይፋ አደረጉ፡፡ አዲሱ አሠራር በቀጣይ ወራት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ዕድሜ የሚያረጋግጠው አሠራር መዘርጋት ያስፈለገው ታዳጊዎች ከእውናዊው ዓለም እየራቁ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ መድረኩ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ የገለጹት አንቶኒ አልባኒዝ፤ የሚዲያ አማራጩ ሕጻናትን ከእውናዊው ዓለም ከማቆራረጡ በተጨማሪ ከእውነተኛ ጓደኞቻቸው ጭምር እየነጠለ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡ አያይዘውም በማኅበራዊ ሚዲያ ምክንያት ወላጆች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለማቀብ እድሜን የሚያረጋግት አሠራር ልትዘረጋ መሆኑን ያስታወቀችው አውስትራሊያ፤ ከባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ወዲህ በሕዝብ ትምሕርት ቤቶች ‘ስማርት’ ስልኮች በተማሪዎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እገዳ ጥላለች፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ እቀባውን ተከትሎ በሀገሪቱ የተለያዩ አስተያየቶች እየተስተናገዱ እንደሚገኝ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

የሕዝብ አስተያየት የሚሰበስበው “ዩጎቭ” ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት መሠረት፤ 61 በመቶ አውስትራሊያዊያን ከ17 ዓመት በታች የሚገኙ ታዳጊዎች የማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ እቀባ እንዲጣልባቸው ፍላጎት አላቸው፡፡ ሆኖም አንዳንድ በጉዳዩ ላይ ጥናት የሚሠሩ ተመራማሪዎች ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ ሙሉ ለሙሉ ማገድ ተዘዋዋሪ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚል መከራከሪያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

 ተመራማሪዎቹ በመከራከሪያቸው ያቀረቡት ሁሉንም የማኅበራዊ ሚዲያዎች ማገድ ታዳጊዎች ጠቃሚ የሚባሉትንም ጭምር ለመጠቀም እንዳይችሉ ያደርጋል የሚል መሆኑን የአልጀዚራ ዘገባ ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም የማኅበራዊ ሚዲያዎቹ እገዳ ታዳጊዎች በምሥጢር ሌሎች የግንኑኘት አማራጮችን ማለትም ‘ቪፒኤ’ን የሚሰኙትን የእቀባ ማለፊያዎች እንዲጠቀሙ ሊያደርግ እንደሚችልም ሥጋታቸውን አጋርተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለታዳጊዎች ጎጂ የሚባሉትንም ጭምር እንዲያዩ ሊያደርግ ይችላል የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡

 የታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እያከራከረ በሚገኝባት አውስትራሊያ፤ በግንቦት ወር ዲጂታል አይዲ የተሰኘ አዋጅ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይኸው የዲጂታል አዋጅ የዜጎችን ማንነት በበይነ መረብ ለመለየት የሚያስችል ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ ታዳጊዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩን የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ “ፒው ሪሰርች” የተሰኘ የጥናት ተቋም ባወጣው ጥናት መሠረት ባለፉት ዓመታት በተለይ ቲክቶክ የተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ታዳጊዎችን ይበልጥ የሚስብ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የጥናት ተቋሙ ባወጣው መረጃ መሠረት ታዳጊዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከልክ በላይ በመሳባቸው ከአሜሪካዊያን ታዳጊዎች ውስጥ 54 በመቶው ‘በፍጹም ከማኅበራዊ ሚዲያ ራሳችንን መነጠል አንችልም’ ብለው የሚያምኑ ሆነዋል፡፡

ዕድሜያቸው ከ12-15 የሆኑ በአሜሪካውያን ታዳጊዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በየቀኑ ከሦስት ሰአት በላይ ማኅበራዊ ሚዲያን የሚጠቀሙ ሰዎች ድብርት እና የጭንቀት ምልክቶችን ጨምሮ አሉታዊ የአእምሮ ጤና ውጤቶችን ማለትም እንደ ድብርት እና ጭንቀት ላሉ መታወኮች የመጋለጥ እድላቸው በሁለት እጥፍ ከፍ ይላል፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular