‘ጄዊሽ ክሮኒክል’ መቀመጫውን በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ከተማ ያደረገ ጋዜጣ ነው፡፡ በ1841 የተመሠረተው ጋዜጣው፤ በመላው ዓለም ከሚገኙ የአይሁድ ጋዜጦች ሁሉ የኅትመት ብርሃን ዕያየ የዘለቀ ዕድሜ ጠገብ ጋዜጣ ነው ይባልለታል፡፡ ሆኖም ወደ ሁለት መቶ ዓመት እየተጠጋ የሚገኘው ጋዜጣው እንደ ዕድሜው መሆን ተስኖት ከሰሞኑ በቅሌት ተዘፍቋል፡፡
ጋዜጣውን ቅሌት ውስጥ የዘፈቀው ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ ጋዛን የተመለከቱ በፈጠራ የተሞሉ ዜናዎችን እያተመ መቆየቱ በመጋለጡ ነው፡፡ ጄዊሽ ክሮኒክል የፈጠራ ዘገባዎቹን የሚያትመው ‘ኤሎን ፔሪ’ በተሰኘ የዘጋቢ ሥም ነበር፡፡ ስለ ጉዳዩ የሚጽፉ እንዳሉት፤ የተጠቀሰው ‘ዘጋቢ’ በጋዜጠኝነት የሚታወቅ አይደለም፡፡
እንደ ዘገባዎቹ ከሆነ የኤሎን ፔሪ የፈጠራ ዘገባ በመገናኛ ብዙኃን በጥርጣሬ መታየት የጀመረው፤ በጋዛ የሚኖሩት የሐማሱ አዲስ መሪ የሕያ ሲንዋር በቡድኑ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሠፋሪዎችን ይዘው ወደ ኢራን ሊጓዙ ነው የሚል ዜና ካስነበበ በኋላ ነው፡፡
ጋዜጣው የሕያ ሲናዋር ሠፋሪዎቹን ይዘው ሊወጡበት ነው ያለው የጋዛ ክፍል በግብጽ ድንበር የሚገኘው የእስራኤል ባለሥልጣናት ፊላዴልፊ ኮሪዶር ሲሉ በሚጠሩት መሬት በኩል ነው፡፡ የጄዊሽ ክሮኒክሉ ‘ኤሎን ፔሪ’ ያሠራጫቸው ዜናዎች ስለ ጉዳዩ ተናግረዋል በሚባሉ ‘የምናብ ባለሥልጣናት’ ዋቢ የሚጠቀስበት ነበር፡፡
ስለ ጉዳዩ የጻፉ እንዳሉት ዜናው እንዲጎላ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤንያሚን ኔታንያሁ በወቅቱ ከሐማስ ጋር በነበረው ድርድር የያዘውን አቋም ለማጠናከር በሚል ነው፡፡ ዜናውን በተመለከተ የእስራኤል ወታደራዊ ኃላፊዎች የተቃርኖ አስተያየት መሰንዘራቸውም ጥርጣሬው ይበልጥ በመጠን እንዲጨምር አድርጎታል፡፡ ዜናዎቹ ላይ ምርመራ ያደረጉ በመጨረሻ በሰጧቸው ድምዳሜዎች እንደገለጹት፤ የጄዊሽ ክሮኒክል ዘገባዎች የቤንያሚን ኔታንያሁ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚያደርጉት ሆን ብሎ የተሳሳተ መረጃ የማሠራጨት ዘመቻ አካል ነው፡፡
ይህንኑ ተከትሎ አራት ዕውቅ የጋዜጣው አምደኞች በገዛ ፍቃዳቸው ጄዊሽ ክሮኒክል ላይ መጻፍ ይብቃን በማለት መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ከጋዜጣው አምደኝነት ከለቀቁት መካከል ለ26 ዓመታት ለጋዜጣው የጻፈው አንጋፋው የዘ ጋርዲያን ጸሐፊ ጆናታን ፍሬድላንድ ይገኝበታል፡፡ ጸሐፊው ጋዜጣው የተዘፈቀበት ቅሌት አሳፋሪ መሆኑን በኤክስ ገጹ አስፍሯል፡፡ ጋዜጣው የፈጠራ ዜናዎቹን ባለፈው ቅዳሜ ከድረ ገጹ ላይ ማንሳቱን ቢገልጽም፤ ሌሎች ሦስት አምደኞችም በቃን ብለው በፍቃዳቸው ሥራ ለቀዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












