የአሜሪካ መንግሥት ለእስራኤሉ ለቤንያሚን ኔታንያሁ ጦር የሚሰጠውን ድጋፍ ማቆም አለበት ያሉት የሀገሪቱ ሴናተር በርኒ ሳንደርስ ናቸው፡፡ ሴናተሩ የእስራኤል ወታደሮች የሚፈጽሙትን የንጹሐንን ግድያ አውግዘዋል፡፡
ሴናተር በርኒ ሳንደርስ ሀገራቸው ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ እንድታቆም ሲጠይቁ፤ እስራኤል በተያዘው ሳምንት በጋዛ የፈጸመችውን የንጹሐን ግድያ በማንሳት ድርጊቱ በቃ ሊባል የሚገባው መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ሳንደርስ ተቃውሟቸውን ሲያሠፍሩ በተያዘው ሳምንት ቀናት ብቻ በዌስት ባንክ አካባቢ በአጠቃላይ 33 ንጹሐን ተገድለዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው የነበረ ትምሕርት ቤት ላይ በእስራኤል በተሰነዘረው ጥቃት ከተገደሉት ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የረድኤት ሠራተኞችም ጭምር እንዳሉበት ገልጸዋል፡፡
የበርኒ ሳንደርስ አስተያየት የመጣው፤ ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ወታደሮች የቱርክ መሠረት ያላትን አሜሪካዊ አክቲቪስት አይሴኑር ኤዝጊን በተቃውሞ ሠልፍ ላይ መግደላቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ከግድያው በኋላ የተነሳው ተቃውሞ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጭምር አስተያየት እንዲሰጡ ያስገደደ ሆኖ አልፏል፡፡
በሀገሯ ሴናተር በርኒ ሳንደርስ ለእስራኤል የምትሰጠውን ድጋፍ እንድታቆም ጥሪ የቀረበላት አሜሪካ፤ ከዓለም ሀገራት ለእስራኤል ከፍተኛውን የጦር መሣሪያ የምትልክ ሀገር ነች፡፡ እስራኤል ከምትቀበላቸው የጦር መሣሪያዎች መካከል 69 በመቶው ከአሜሪካ የሚገቡ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አሜሪካ ከፍተኛውን የጦር መሣሪያ የምታስታጥቀው ቤንያሚን ኔታንያሁ ወታደሮች ባለፉት አስራ አንድ ወራት ብቻ በጋዛ የ41 ሺሕ ንጹሐንን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት እናቶች እና ሕጻናት ናቸው፡፡












