በማሌዥያ የኦቲዝም እክል ያለበት የ26 ዓመት የቁርኣን ሒፍዝ አጠናቀቀ፡፡ ወጣቱ የመጀመሪያ ዲግሪውን በቁርኣን ጥናት ተምሮ ማጠናቀቅም ችሏል፡፡
በማሌዥያ የኦቲዝም እክል ያለበት የ26 ዓመት የቁርኣን ሒፍዝ ማጠናቀቁን የገለጹት፤ የዩኒቨርሲቲ ኢስላም ፓሃንግ ሡልጣን አሕመድ ሻህ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ ኃላፊዎች እንደተናገሩት የመጀመሪያ ዲግሪውን በቁርኣን ጥናት ያጠናቀቀው ናቁብ አጃመል መሐመድ የሚባል ተማሪ ነው፡፡ እንደ ኃላፊዎቹ ከሆነ፤ ወጣቱ ማሌዥያዊ የቁርኣን ጥናት ትምህርቱን ከማጠናቀቁ ባሻገር ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
ናቁብ አጃመል መሐመድ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የቁርኣን ሒፍዝ ጥናቱን ከመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቱ ጋር ጎን ለጎን ሲያካሄድ ነበር፡፡ ወጣቱ ጥናቱን ማጠናቀቁን ተከትሎ ለዚህ ደረጃ ለመድረሱ የወላጆቹ እንዲሁም የመምህራኑ ሚና ከፍተኛ እንደነበር በመጥቀስ ምሥጋና አቅርቧል፡፡ ናቁብ “ያለ ወላጆቼና እና መምህራን ድጋፍ አሁን ያገኘሁትን ማሳካት አዳጋች ነበር” ሲል ተናግሯል፡፡
የወጣቱ ወላጆች የሆኑት መሐመድ ጀማል ናስር እና እናት አኒታ ኢልያስ፤ ልጃቸው ከሰዎች ጋር በሚያወራበት ጊዜ ፊት ለፊት እየተያየ መነጋገር ይቸግረው እንደነበር በማስታወስ፤ የሀገሬውን ቋንቋ ማላይን በመጠኑ መናገር የቻለውም በዘጠኝ ዐመቱ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በአንጻሩ የዐረቢኛ እና እንግሊዝኛ ቃላት እውቀቱ አስገራሚ እንደነበር አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ማሌዥያዊው የቁርኣን ሐፊዝ የሚቸገርበት ኦቲዝም ዘላቂ የአዕምሮ እድገት ውስንነት እክል መሆኑን የሕክምና ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ ኦቲዝም አንዳንድ ሕፃናትን ከማኅበራዊ ሕይወታቸው እንደሚነጥላቸው እንዲሁም ያልተለመደ ባሕርይ እንዲያሳዩ ያደርጋቸዋል ይባላል፡፡
የኦቲዝም እክል ያለባቸው አንዳንድ ሕፃናት ያልተለመደ ባሕርይ ቢያሳዩም፤ ለየት ያለ የመማር ችሎታ ያላቸውና የመረዳት ክሕሎታቸው የላቀና ለየት ያለ እንደሆነም ሐኪሞች ይናገራሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












