የኢፌዴሪ ትምሕርት ሚኒስቴር በ2016 ለ12ኛ ክፍል ፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች መካከል አጠቃላይ ፈተናውን ያለፉ ተማሪዎች 5.4 በመቶ መሆናቸውን በዛሬው እለት አስታወቀ፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ይህንኑ ይፋ አድርገዋል፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዛሬ ሰኞ ጳጉሜን 3/2016 በሰጡት በሰጡት መግለጫ፤ በዘንድሮው ዓመት ለ12ኛ ክፍል ፈተና የተቀመጡ ተማሪዎች አጠቃላይ ቁጥር 674 ሺሕ 823 መሆኑን በማስታወስ፤ ከእነዚህ ተፈታኞች መካከል 36 ሺሕ 409 ተማሪዎች ማለፊያ ነጥብ መስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
የትምሕርት ሚኒስትሩ በ12ኛ ክፍል ፈተና የተመዘገበውን ውጤት ከአምናው ብልጫ ያለው ነው ብለዋል፡፡ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) በማብራሪያቸው ባለፈው የ2015 የትምህርት ዘመን ለፈተና የተቀመጡት ተማሪዎች አሐዝ 845 ሺህ 699 እንደነበር ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ውስጥ ማለፊያ ነጥብ ማስመዝገብ የቻሉትም 3.2 በመቶው ብቻ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ ይህ ቁጥር በተያዘው ዓመት በ2.1 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡
የትምሕርት ሚኒስቴር በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበባቸው ትምሕርት ቤቶች እንዲሁም የትምህርት ዐይነቶች ዝርዝር ይፋ የተደረገበት ነው፡፡ በዚህም በዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው በትግራይ ክልል ቀላሚኖ ትምሕርት ቤት መሆኑን የገለጸው ትምሕርት ሚኒስቴር፣ ከ700 በተሰጠው ፈተና 675 ውጤት መመዝገቡን አሳውቋል፡፡ በትግራይ ክልል በወንድ ተማሪ ከቀላሚኖ የተመዘገበው 675 ከፍተኛ ውጤት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ ነው ተብሏል፡፡
በሌሎች ክልሎች ፈተናው የታረመው 600 መሆኑን ያስታወሰው የትምሕርት ሚኒስቴር፤ በዚህ አግባብ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት 575 እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
በትምሕርት ቤቶች አዳሪ ትምሕርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን የተገለጸ ሲሆን፣ ኢንተርናሽናል ኮሚኒቲ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የግል ትምሕርት ቤቶች በቀጣይነት ተቀምጠዋል፡፡ በሌላ በኩል በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮሮው ዓመት 1 ሺህ 363 ትምሕርት ቤቶች ምንም ተማሪ እንዳላሳለፉም የትምሕርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል፡፡
ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ሀገራዊ አማካኝ ውጤት 29 ነጥብ 76 መሆኑን የጠቀሱት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፤ የወንዶች አማካይ ውጤት 30.66 እንዲሁም የሴቶች አማካይ ውጤት 28 ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል፡፡ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 10 ሺሕ 690 ተማሪዎች በማሳለፍ ከፍተኛውን ሥፍራ ይዟል። በዚህ ሥሌት መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካስፈተናቸው ተማሪዎች 21.4 በመቶው ማለፍ ችለዋል፡፡ በሀገር ደረጃ ከ600 ከተፈተኑት ውስጥ 575 ከተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም ከማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 538 ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል። በተፈጥሮም በማህበራዊ ሳይንስም ትልቅ ውጤት የመጣው በሴቶች ነው።
በኢትዮጵያ ከ2014 አንስቶ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የሚሰጠው በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር በ2016 በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ኦንላይን ፈተና መስጠቱም የሚታወስ ነው፡፡ በኦንላይን ከተፈተኑ ተማሪዎች 26.6 በመቶ የሚሆኑት ማለፊያ ውጤት ማስመዝገባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡












