በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው መስሊሞች ማኅበር በክረምት መርሐ ግብር በምልክት ቋንቋ ዲናዊ ትምሕርት ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዐት አከናወነ። በሥነ ሥርዐቱ ላይ ማኅበሩ ተደራሽነቱን ለማሥፋት የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል።
በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው መስሊሞች ማኅበር በክረምት መርሐ ግብር በምልክት ቋንቋ ዲናዊ ትምሕርት ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዐት ያከናወነው ዛሬ እሑድ ጳጉሜን 3/2016 ነው። በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አዳራሽ በተከናወነው የምርቃት ሥነ ሥርዐት ላይ ዕውቅ የእስልምና ሃይማኖት መምሕራን እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በክረምቱ ወራት የዲን ትምሕርት የተከታተሉ መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዐት በይፋ ተከናውኗል። ተማሪዎቹ በክረምት ቆይታቸው ሲከታተሉ የቆዩተ ዲናዊ ትምሕርቶችን እንዲሁም ቁርኣን መሆኑ ተገልጿል።

መስማት የተሳናቸው ተማሪዎችን ያስመረቀው ማኅበሩ፣ በአዲስ አበባ አወሊያ ትምሕርት ቤት ፒያሳ ቅርንጫፍ በሳምንቱ መጨረሻ ለአንድ ቀን እንዲሁም በከተማዋ በ11 መስጂዶች የክረምት መርሐ ግብር በማዘጋጀት ሳምንቱን በሙሉ እያስቀራ መሆኑንም አስታውቋል። በዛሬው እለት በተከናወነው ሥነ ሥርዐት ላይ ማኅበሩ ተደራሽነቱን ለማሥፋት ማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።
በኢትዮጵያ ወደ አምስት ሚሊዮን ገደማ መስማት የተሳናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚገኙ ይገመታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ መስማት የተሳናቸው ሳምንት የሚከበረውም በመስከረም ወር እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ይኸው መስማት የተሳናቸው ሳምንት ከሁለት ቀናት በሚጀምረው መስከረም ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ66ኛ ጊዜ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ እንደሚከበር የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ያወጣው መረጃ ያመለክታል።












