በኢንዶኔዥያ ጃካርታ ከተማ ሒጃብ ማውለቅን ለሥራ ቅጥር መሥፈርት አድርጎ ያስቀመጠው ሆስፒታል ይቅርታ ለመጠየቅ ተገደደ፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሔድ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡
ሒጃብን ማውለቅ ለሥራ ቅጥር መሥፈርት አድርጎ ያስቀመጠው በደቡባዊ ጃካርታ የሚገኘው ሜዲስትራ ሆስፒታል ነው፡፡ በሆስፒታሉ ውስጥ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ዲያኒ ካርቲኒ፤ የሥራ ቅጥር ሲወጣ ሴት አመልካቾች ማመልከት የሚችሉት ሒጃባቸውን ለማውለቅ ሲስማሙ እንደሆነ መጠቀሱን አጋልጠዋል፡፡ ዶክተር ዲያኒ ካርቲኒ ይኸው ድርጊት በረዳት ሐኪሞቻቸው ቅጥር ወቅት እንዲሁም እርሳቸው በሚያውቋቸው የሥራ ቅጥር ሲወጣ ያመለከቱ የቅርብ ሰዎች ላይ ጭምር መፈጸሙንም ይፋ አድርገዋል፡፡
ዶክተር ዲያኒ ካርቲኒ ጉዳዩን ባጋለጡበት ደብዳቤ፤ ለሥራ ቅጥር እንደዚህ ዐይነት አግላይ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን “ኋላ ቀር ነው” ሲሉ መተቸታቸውን “ሪፑብሊካ” የተሰኘው የኢንዶኔዥያ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
ጉዳዩ መጋለጡን ተከትሎ ዳይሬክተሩ አጉንግ አጉስት ቡዲሳትሪያ፤ በድርጊቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ድርጊቱ በቀጣይ በተመሳሳይ እንዳይደገም ሆስፒታሉ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ የሆስፒታሉ ባልደረቦች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ጠቁመው፤ የሥራ ቅጥር ቃለ መጠይቅ ሲያከናውኑ የነበሩ ግለሰቦች ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
በሆስፒታሉ ይህ ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ የኢንዶኔዥያ ፖለቲከኞች በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሔድ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚሁ ፖለቲከኞች መካከል የሆኑት የጃካርታ ክልል የምክር ቤት ቃል አቀባይ አሕመድ ያኒ፣ የክልሉ ጤና ቢሮ በጉዳዩ ላይ ምርምራ እንዲጀምር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የኢስላሚክ ፕሮስፔረስ ጀሰቲስ ፓርቲ አባሉ ያኒ፣ ሰዎች ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዳይፈጽሙ የሚያደርግ የትኛውም ፖሊሲ ሊጫንባቸው አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
በጃካርታ ከተማ የሚገኘው ሜዲስትራ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከሠላሳ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)