አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቀጣዩ 2017 የትምህርት ዘመን ጀምሮ አዲስ አሠራር ሊተገብር መሆኑን አስታወቀ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚገቡ አዲስ የቅድመ ምረቃ እና ድሕረ ምረቃ ተማሪዎች የተዘጋጀውን የመወዳደሪያ ነጥብ፣ የመግቢያ ፈተና እንዲሁም ሌሎች መስፈርቶችን ማሟላት ይገባቸዋል ተብሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች ይህን ያስታወቁት ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 27/2016 ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ነው፡፡ በዛሬው ምለጫ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ተግባራዊ በሚያደርገው አዲስ የተማሪዎች ቅበላ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ማስተማሪያ ተቋም እንደሚያደርገው ኃላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው የሚከተለው አዲስ አሠራር ተቋሙን የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ማስተማሪያ ተቋም ያደርገዋል ብለዋል፡፡ አዲሱ አሠራር የሚተገበረው በዩኒቨርሲቲው በሚገቡ አዲስ የቅድመ ምረቃ እና ድህረ ምረቃ ተማሪዎች መሆኑንም ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ገልጸዋል፡፡
ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት በትምህርታቸው ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች የተዘጋጀውን የመወዳደሪያ ነጥብ፣ የመግቢያ ፈተና እንዲሁም ሌሎች መስፈርቶችን ማሟላት የማይችሉ ከሆነ፤ ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደማይገቡ ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ፍትሐዊ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት እንዲሁም ኢትዮጵያ በመጪው ዘመን የምትፈልገውን ብቁ ምሩቃንን ለማፍራት ያግዛል የታለው አሠራር፤ በመንግሥት ወጪ የሚሸፈን የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) እና በግል ወጪን በመሸፈን የተማሪዎችን ስብጥር በጠበቀ መልኩ ማስተናገድ እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረጸ ነው ተብሏል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሐምሌ 2015 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝ ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ተወያይቶ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)