ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጠው ዘምዘም ባንክ፣ ሰባት ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ማሰባሰብ መቻሉን አስታወቀ። የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 2.1 ቢሊዮን መድረሱ ተገልጿል።
ዘምዘም ባንክ ሰባት ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ማሰባሰብ መቻሉን ይፋ ያደረገው፣ ዛሬ እሑድ ነሐሴ 26/2016 ከ5 ሺሕ በላይ ከሚሆኑ ባለአክስዮኖች፣ ደንበኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ሚሊንየም አዳራሽ ባካሔደው ውይይት ወቅት ነው።
ውይይቱ ዘምዘም ባንክ ከምሥረታ ወቅት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለፈባቸው ጉዞዎች፣ ያሳካቸው ግቦች፣ በመንግሥት እየተተገበሩ ያሉ የፋይናንሺያል ሪፎርም መልካም አጋጣሚዎች እና በባንኩ ቀጣይ ጉዞ ላይ ያተኮረ ነበር።
በዚህ ወቅት ባንኩ ሥራ ከጀመረ አንስቶ በመላ ሀገሪቱ ላሉ ማኅበረሰቦች አክስዮን በመሸጥ በአሁኑ ወቅት ከአስራ ስድስት ሺሕ በላይ ባለአክስዮኖች እንዳሉት ገልጿል። የተከፈለ ካፒታሉም ብር 2.1 ቢሊዮን መድረሱን የባንኩ ኃላፊዎች በዚሁ መድረክ ላይ ተናግረዋል።
የባንኩ ኃላፊዎች በዛሬው እለት ባቀረቡት ገለፃ፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ሲናገሩ የስትራቴጅክ እቅዶችን ከግብ ለማድረስ እንዲቻል ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር የማሳደግ ግብ መቀመጡንም ጠቁመዋል። ይህን ለማሳካት አሳታፊነቱን በማስፋት ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እና ዲያስፖራዎች አክስዮን እንደሚሸጡ ገልፀዋል።