የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የመውሊድ በዓል “የሰላሙ ነቢይ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡ የምክር ቤቱ ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ፤ የረቢዐል አወል ወር እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚሰጡ ትምህርቶች እና ዳዕዋዎች በዚሁ ርእስ ላይ እንዲያጠነጥኑ ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ መውለድ አከባበር ብሔራዊ ኮሚቴ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 23/2016 በሰጠው መግለጫ፤ መውሊድ የሚከበረው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት የተቋቋመበት 50ኛ ዓመት የመውሊድ እለት በመሆኑ መውሊድ በኢትዮጵያ ደረጃ 50ኛ ዓመት ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች ይኖራሉ ብሏል፡፡ በዛሬው መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ “የሰላሙ ነቢይ” በሚል መሪ ቃል ከሚከበረው የመውሊድ በአል ጎን ለጎን የረቢዕል አወል ወር እስከሚጠናቀቅ ድረስ ትምህርቶች እና ዳዕዋዎች በዚሁ ርዕስ ላይ እንዲያጠነጥኑ ውሳኔ መተላለፉንም ይፋ አድርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዓሉ በሚከበርበት ወቅት፤ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሠማሩ ተቋማት ጉብኝት እንደሚደረግ የገለጸው ኮሚቴው፤ ሕፃናት እና ታዳጊዎችን የሚያሳትፍ መሰናዶ፣ የመንዙማ ጥናት የሚቀርብበት መድረክ እንዲሁም የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የዝግጅቱ አካል እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡ ኮሚቴው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የሚደረገው በአወሊያ ነስር ትምህርት ቤት እንደሚሆንም አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ ኅብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ለኢትዮጵያ ሰላም ዱዓ በማድረግ የነቢያዊ ፈለጋቸውን በመከተል ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝቧል፡፡ የ1499ኛው የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የመውሊድ በዓል መስከረም 5/2017 ይከበራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)