የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወነ በሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሒደት፤ በተለያዩ አካባቢዎች ሙስሊሞችን በመወከል ተሳታፊ የሚሆኑ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲያስተጋቡ ተጠየቀ፡፡ በሲዳማ ክልል የሚካሔደው የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ በነገው እለት ይጀመራል ተብሎ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወነ በሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሒደት፤ ሙስሊሞችን በመወከል ተሳታፊ የሚሆኑ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲያስተጋቡ የጠየቁት በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የእቅድ ጥናትና ፖሊሲ አገልግሎት ኃላፊና ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በተገናኘ አንደኛው አስተባባሪ የሆኑት ሐጂ ኑረዲን ጀማል ናቸው፡፡ አስተባባሪው ይህን ያሉት በነገው እለት የሚጀመረውን የሲዳማ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በተመለከተ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናገሩበት ወቅት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከነገ ረቡዕ ነሐሴ 22/2016 ጀምሮ በሲዳማ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ሊያካሄድ መሆኑን ያስታወቀው በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ነው፡፡ ኮሚሽነሮቹ በክልሉ የሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ለሰባት ቀናት እንደሚቆይ አስረድተዋል፡፡
በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ላይ በቀጥታ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በመወከል ሰባት ግለሰቦች እንደሚሳተፉ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የእቅድ ጥናትና ፖሊሲ አገልግሎት ኃላፊ ሐጂ ኑረዲን ጀማል አብራርተዋል፡፡ ሐጂ ኑረዲን ከሰባቱ ተወካዮች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት በኩል ሦስት ተወካዮች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡ ኃላፊው በነገው እለት የአጀንዳ ማሰባሰብ በሚጀመርበት ሲዳማ ክልል ከዚህ ቀደም ከውክልና ጋር በተገናኘ ቅሬታ መቅረቡን በማስታወስ፤ አሁንም ቢሆን ውክልናው አጥጋቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሲዳማ ክልል የሚካሄደው የምክክር መድረክ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወካዮች በተጨማሪ የተለያዩ የህብረተሰብ ወኪሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አካላት ወኪሎች፣ የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወኪሎች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ወኪሎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ መድረክ ተወካዮቹ ተመካክረው ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎችን ለይተው ለኮሚሽኑ እንደሚያስረክቡ ሀገራዊ ምክክር አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የእቅድ ጥናትና ፖሊሲ አገልግሎት ኃላፊ ሐጂ ኑረዲን በዚህ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሙስሊም የቀረቡ ዘጠኙን አጀንዳዎች እንዲያንጸባርቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለምክክር ሒደት የሚቀርቡ የሀገሪቱን ሙስሊሞች አጀንዳዎች ለምክክር ኮሚሽን ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ባቀረበው ሰነድ ዘጠኝ አጀንዳዎች በአጀንዳነት ቀርበዋል፡፡ እነዚህም ታሪክና ትርክት፣ ሀገራዊና ሕዝባዊ ምልክቶች፣ የሲቪል መብቶችና ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል፣ የሕዳጣን (Minority) መብት፣ የኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል መሆን፣ የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት፣ ለሙስሊም ጠልነት ዕውቅና መስጠት እና ማስተካከል፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንዲሁም አካታች ኢኮኖሚና ፋይናንስ ማስፈን የሚሉት ናቸው።
በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ውይይት ለማካሄድ በሒደት ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታኅሣሥ 2014 በጸደቀ የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ በመንግሥት እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮችን እንደሚለይ አስፍሯል። (ሚንበር ቲቪ)