በአዲስ አበባ ከተማ ይገነባል ተብሎ እቅድ የተያዘለት የነጃሺ መስጂድ እና እስላማዊ ማዕከል የግንባታ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡ የግንባታውን ሒደት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የነጃሺ እስላማዊ ማዕከል ግንባታ ዐብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ፤ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ተናግረዋል፡፡
የነጃሺ መስጂድ እና እስላማዊ ማዕከል የግንባታ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር ለ“ሚንበር ቲቪ” የተናገሩት ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ የግንባታ ሥራውን ለመጀመር በሚያስፈልገው ቅድመ ዝግጅት የግንባታ ፍቃድ ማውጣትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችም በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የግንባታ ፍቃድ ማውጣት መከናወኑን የጠቆሙት ኡስታዝ አቡበከር፤ “የአፈር ምርመራ እና የኢ-ካርታ ማውጣት ሒደት” ጎን ለጎን እየተሠራበት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የግንባታ ሒደቱ በቅርቡ ይጀመራል የተባለው የነጃሺ መስጂድ እና እስላማዊ ማዕከል በሚያዝያ 2012 በመንግሥት በተሰጠ 30 ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ የነጃሺ እስላማዊ ማዕከል ግንባታ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ይፋ ያደረገው የባለሞያ የመጀመሪያ ደረጃ ግምት ያመለክታል፡፡
የማዕከልን ግንባታ የበጀት ምንጭ በተመለከተ ከዚህ ቀደም በሳዑዲ ዐረቢያ መቀመጫውን ያደረገው የዓለም ሙስሊም ሊግ በዋና ጸሐፊው ዶክተር ሙሐመድ ዓብዱልከሪም ዒሳ በኩል ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ዶክተር ሙሐመድ ዓብዱልከሪም ዒሳ የግንባታውን በጀት ለመሸፈን ቃል የገቡት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡
ይኸው እስላማዊ ተቋም በጀቱን ለመሸፈን የገባውን ቃል አሁንም ድረስ የተጠበቀ መሆኑን ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ አረጋግጠዋል፡፡ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቃቸውን ተከትሎም፤ ለዓለም ሙስሊም ሊግ ጥያቄው ቀርቦ መልካም ምላሽ መገኘቱን በመጥቀስ፤ በአጭር ጊዜ የኢትዮጵያን “ሙስሊሞች ቁመና የሚመጥን” ግንባታ ይካሔዳል ብለዋል፡፡ የኪነ ሕንጻ ንድፉ መጽደቁን ያስታወሱት ኡስታዝ አቡበከር፤ ንድፉን ተግባራዊ ለማድረግ የግንባታ ተቋራጩ ዓለም አቀፍ ልምድ ያለው እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
የነጃሺ መስጂድ እና እስላማዊ ማዕከል የኪነ ሕንጻ ንድፍ በተያዘው ዓመት የካቲት ወር አሸናፊው ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ማዕከሉ ሲገነባ መስጂድ፣ የማኅበረሰብ ማዕከላት እና የንግድ ማዕከል የሚካተትበት ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)