Homeዜናና ወቅታዊዜናበሥልጤ ዞን ጎፍለላ ቀበሌ የተከሰተው ጎርፍ፤ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች በመዛመቱ የተፈናቃይ አባወራዎች...

በሥልጤ ዞን ጎፍለላ ቀበሌ የተከሰተው ጎርፍ፤ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች በመዛመቱ የተፈናቃይ አባወራዎች ቁጥር አንድ ሺሕ ተሻገረ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሥልጤ ዞን ጎፍለላ ቀበሌ የተከሰተው ጎርፍ፤ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች በመዛመቱ የተፈናቃይ አባወራዎች ቁጥር አንድ ሺሕ መሻገሩን የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ አስወቀ፡፡ በዞኑ የተከሰተው ጎርፍ ስድስት ቀበሌዎችን አዳርሷል ተብሏል፡፡

በሥልጤ ዞን ሥልጢ ወረዳ ጎፍለላ ቀበሌ የተከሰተው ጎርፍ፤ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች የተዛመተው ማክሰኞ ነሐሴ 14/2016 የጣለውን ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ተከትሎ መሆኑን የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሊያ ሐሰን ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡ የጎርፍ አደጋው ቀድሞ ከተከሰተበት ጎፍለላ በተጨማሪ በአሹቴ፣ ባሎ ቀሪሶ፣ ምዕራብዬ እየቆጬ፣ ምሥራቅ እየቆጬ እና ሰዳ ጎራ ቀበሌዎችን አዳርሷል፡፡

በዞኑ በቀዳሚው የጎርፍ አደጋ 600 ገደማ አባወራዎች መፈናቀላቸውን ገልጾ የነበረው የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ፣ የተፈናቃይ አባወራዎች ቁጥር ከአንድ ሺሕ መሻገሩን ይፋ አድርጓል፡፡ እነዚህ አባወራዎች የያዙት የሕዝብ ቁጥር ከአምስት ሺሕ በላይ መሆኑን አቶ ሳሊያ ሐሰን አስረድተዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ቀናት በተጨማሪ የተከሰተው ጎርፍ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ባያደርስም፤ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡

በዞኑ በጎርፍ ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት በጊዜያዊ የተፈናቃይ ጣቢያዎችና በአቅራቢያ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ሆኖም የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ተፈናቃዮችን ማስተናገድ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መመሪያ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡ የኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊው የተፈናቃዮቹን የመጠለያ አቅም “ከዞኑ አቅም በላይ ነው” ብለዋል፡፡

የሥልጤ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ ሳሊያ ሐሰን፤ ለጎርፉ መከሰት ምክንያት ነው የሚሉት፤ ጎርፉ በመደበኛነት በሚፈስበት መውረጃ ላይ ከአምስት ዓመት በፊት የተገነባ ግድብ ነው፡፡ ይህን ግድብ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ለማንሳት ጥረት መደረጉን የሚያስታውሱት አቶ ሳሊያ፤ ግድቡ ሲነሳ ደለል በመሥራቱ አካባቢዎቹ ለጎርፍ ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊው ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ላለመነሳቱ ምክንያቱ “የተመደበው በጀት አልቋል” በመባሉ መሆኑ እንደተነገራቸውም ይገልጻሉ፡፡ በቀጣይ በዞኑ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት መፍትሔው ደለሉን ማንሳት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሥልጤ ዞን የተከሰተውን ጎርፍ ተከትሎ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮችም በቂ ድጋፍ እንዳልተደረገ የገለጹት ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ የዞኑ ኃላፊዎች “አሳሳቢ ነው” ያሉትን አደጋ ለመከላከል ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular