የአሜሪካው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ኤክስ (የቀድሞ ትዊተር)፤ ለፍልስጤማዊያን በሚሰጠው ድጋፍ የሚታወቀውን የግብጻዊውን ኮሜዲያን ባሲም ዩሱፍን አካውንት እንዳይታይ ማድረጉ መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ነዋሪነቱን አሜሪካ ያደረገው ግብጻዊው ኮሜዲያን፤ በመጨረሻ ጽሑፉ “ፀረ ሴማዊነት” አላግባብ ሰዎችን ፀጥ ለማሰኘት እንዲሁም ለማሸማቀቅ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ሲል ኮንኗል፡፡
ኤክስ ማኅበራዊ ትስስር መድረክ፤ የባሲም ዩሱፍን ገጽ እንዳይታ ካደረገ 16 ሰዓታት ተቆጥረዋል፡፡ ዋና መቀመጫውን ሳንፍራንሲስኮ ያደረገው ኤክስ፤ እስካሁን ድረስ የኮሜዲያን ባሲም ዩሱፍን ገጽ ለምን እንዳይታይ እንዳደረገ የገለጸው ነገር የለም፡፡ ባሲም ዩሱፍ በመጨረሻ በገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ፤ በፅዮናዊያን አላግባብ ሰዎችን ፀጥ ለማሰኘት እንዲሁም ለማሸማቀቅ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ስላለው “ፀረ ሴማዊነተ” ተከታዮቹ ሐሳባቸውን እንዲሰጡት ጠይቆ ነበር፡፡
ሆኖም ይህን ጽሑፍ ካሠፈረ ከጥቂት ቆይታ በኋላ 12 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት የኤክስ አካውንቱ እንዳታይ ተደርጓል፡፡
በዜግነት አሜሪካዊው የግብጽ ተወላጅ ባሲም ዩሱፍ፤ በተለይ በተያዘው ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ እስራኤል በጋዛ መሰንዘር የጀመረችውን ጥቃት ተከትሎ፤ ከብሪታኒያዊው ጋዜጠኛ ፒርስ ሞርጋን ጋር ባደረገው ስላቅ የሞላው ቃለ ምልልሱ ይበልጥ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ለመሳብ ችሎ ነበር፡፡ ባሲም በዚህ ቆይታው የእስራኤልን ጥቃት በፅኑ በማውገዝ፤ ለፍልስጤማዊያን ድምጽ ሆኗል በሚል ሙገሳ ይቀርብለታል፡፡
በሙያ የቀዶ ጥገና ሐኪም የሆነው ባሲም ዩሱፍ፤ እ.አ.አ ከ2015 አንስቶ መኖሪያውን በአሜሪካ አድርጓል፡፡ ባሲም ዩሱፍ እ.አ.አ በ2013 የታይም መጽሔት 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ የዓለማችን ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካቷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












