Homeዜናና ወቅታዊዜናበሥልጤ ዞን በተከሰተ ጎርፍ 600 ገደማ አባወራዎች ተፈናቀሉ

በሥልጤ ዞን በተከሰተ ጎርፍ 600 ገደማ አባወራዎች ተፈናቀሉ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥልጤ ዞን በተከሰተ ጎርፍ፤ 600 ገደማ አባወራዎች መፈናቀላቸውን የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ አስታወቀ፡፡ የኮሚኒኬሽን ቢሮው እንዳለው ከሆነ፤ በጎርፉ በከፍተኛ መጠን የተጠቃው በሥልጢ ወረዳ የሚገኘው ጎፍለላ ቀበሌ ነው፡፡

በዞኑ የተከሰተው ጎርፍ ወደ አጎራባች ቀበሌዎች በመዛመት 600 ገደማ አባወራዎች መፈናቀላቸውን የሥልጤ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሊያ ሐሰን ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው ጎርፉ በሥፋት ተከስቶበታል ባሉት ጎፍለላ ቀበሌ 330 አባወራዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ አካባቢ የነበረ ሰብል ሙሉ ለሙሉ ወድሟል ተብሏል፡፡ በዚያው አካባቢ አሹቴ በሚባል ቀበሌ እንዲሁም በሌሎችም ሦስት ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በጎርፉ ለመፈናቀል መገደዳቸውን አቶ አቶ ሳሊያ ተናግረዋል፡፡

የሥልጢ ወረዳ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት 

በዞኑ በጎርፍ ምክንያት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት በጊዜያዊ የተፈናቃይ ጣቢያዎችና በአቅራቢያ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው እንደሚገኙ ተሰምቷል፡፡ በዞኑ ኃላፊዎች በዘንድሮው ክረምት በመጠን እንደጨመረ የተነገረለት ጎርፍ፤ ባለፉት ዓመታት በተመሳሳይ ተከስቶ በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

የሥልጤ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳሊያ ሐሰን

የሥልጤ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ ሳሊያ ሐሰን፤ ለጎርፉ መከሰት ምክንያት ነው የሚሉት ጎርፉ በመደበኛነት በሚፈስበት መውረጃ ላይ ከአምስት ዓመት በፊት የተገነባ ግድብ ነው፡፡ ይህን ግድብ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ለማንሳት ጥረት መደረጉን የሚያስታውሱት አቶ ሳሊያ፤ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ሊነሳ ባለመቻሉ አካባቢዎቹ ለጎርፍ ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊው ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ላለመነሳቱ ምክንያቱ “የተመደበው በጀት አልቋል” በመባሉ መሆኑ እንደተነገራቸውም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በድንበር አካባቢ አለመግባባት መኖሩንም እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡  


በሥልጤ ዞን በተከሰተው ጎርፍ እስካሁን ድረስ በቤተሰብ ደረጃ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ብዛት ከ1 ሺሕ 600 በላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የወደመው ሰብልም 300 ሄክታር መሬት ላይ ለምቶ የነበረ መሆኑን ጎርፉ የተከሰተት ቀበሌ የሚገኝበት የሥልጢ ወረዳ ሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡

በቀጣይ ተመሳሳይ ጎርፍ ተከስቶ ነዋሪዎች በድጋሚ እንዳይፈናቀሉ መፍትሔው ሙሉ ለሙሉ ሳይነሳ የቀረውን ግድብ እንዲወገድ ማድረግ መሆኑንም የስልጤ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተናግረዋል፡፡ በሥልጤ ዞን የተከሰተውን ጎርፍ ተከትሎ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዮችም በቂ ድጋፍ እንዳልተደረገ የገለጹት ኃላፊው፤ “አሳሳቢ ነው” ያሉትን አደጋ ለመከላከል ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular