የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለመሳተፍ የገንዘብ ዋስትና ላስያዙ ምዕመናን፤ ገንዘብ ተመላሽ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ምክር ቤቱ ሌሎች ተመላሽ ክፍያዎችን የሚወስዱ ምዕመናን በቀጣይ ሣምንት ይስተናገዳሉ ብሏል፡፡
ምክር ቤቱ ባለፈው የሂጅሪ ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ለመሳተፍ ዋስትና ያስያዙ ምዕመናን ገንዘብ መመለስ ጀምሬያለሁ ያለው፤ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ /2016 ነው፡፡ የምክር ቤቱ የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሐጅ ዐብዱልፈታህ ሙሐመድ፤ በዛሬው እለት ገንዘብ ተመላሽ መደረግ ጀምሯል ያሉት ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች በመሆኑ የዋስትና ገንዘብ በማስያዝ ጉዞ እንዲያደርጉ ፍቃድ የተሰጣቸውን ሑጃጅ ነው፡፡

እንደ ምክር ቤቱ መረጃ እነዚህ ምዕመናን በዕድሜያቸው ምክንያት ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ከከፈሉት ገንዘብ ተጨማሪ 160 ሺሕ ብር በዋስትና አስይዘዋል፡፡ ምክር ቤቱ ገንዘብ ተመላሽ ማድረግ መጀመሩን ቢገልጽም፤ ሚንበር ቲቪ ጉዳዩን ከምዕመናን ማረጋገጥ አልቻለም፡፡
በዕድሜ ምክንያት ገንዘብ እንዲያስይዙ ከተደረጉት ውጪ፤ ለሐጅ ሥነ ሥርዐት የተቀመጠውን ሙሉ ክፍያ ቢፈጽሙም፤ በተለያየ ምክንያት ወደ መካ አቅንተው መሳተፍ ያልቻሉ ምዕመናን እንዳሉ ያስታወሱት ኃላፊው፤ ለእነዚህ ምዕመናንም በተመሳሳይ የከፈለት ገንዘብ ተመላሽ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ ምዕመናኑ ለጉዞ ሳይነሱ ሕይወታቸው ያለፈ፣ በፓስፖርት እና በደኅንነት ጉዳዮች የጉዞ መርሐ ግብር ማከናወን ያልቻሉ እንዲሁም በግል ትኬት በመግዛት የተጓዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የእነዚህ ምዕመናን ክፍያ የሚፈጸመው በቀጣዩ ሣምንት እንደሚሆን የጠቆሙት ዐብዱልፈታህ፤ ምዕመናን ማንኛውም ተመላሽ ክፍያ አለን የሚሉ ከሆነ በተመዘገቡባት የሐጅ ጣቢያ ሔደው ማመልከት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮ ጠቅላይ ምክር ቤት ተመዝግበው ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ያቀኑ ምዕመናን ቁጥር 12 ሺሕ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ለሐጅ ከተጓዙ ምዕመናን መካከል አስር ኢትዮጵያዊያን ወደ አኺራ መሻገራቸውንም ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












