በቱርክዬ አደራዳሪነት ለሚካሔደው የወደብ ውይይት አንካራ ያመሩት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አፅቀሥላሴ እና የሶማሊያ አቻቸው አሕመድ ሙዓሊም ፈቂ፤ ፊት ለፊት መነጋገር ሳይችሉ መቅረታቸው ተሰምቷል፡፡ የቱርክዬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፋይደን ትናንት ሰኞ ሁለቱን ሚኒስትሮች ለሁለት ጊዜ በተናጠል አነጋግረዋል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በወደብ ጉዳይ ከሶማሊያ ጋር የምታደርገው ውይይት ትናንት ሰኞ ነሐሴ 6/2016 የተካሔደው ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአንካራ የተከናወነው ውይይት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በአካል ሳይገናኙ የቀሩበት እንዲሁም ከስምምነት ያልተደረሰበት ቢሆንም፤ ሀገራቱ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ባለማሳየታቸው በሁለተኛው ዙር የሚከናወነው ውይይት ለውጥ ያሳያል በሚል ሲነገር ነበር፡፡
ሆኖም ትናንት የነበረውን ውይይት በተመለከተ የወጡ ዘገባዎች በዚህ ዙር ውይይት እንደ ቀዳሚው ሁሉ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ እና አሕመድ ሙዓሊም ፊት ለፊት መነጋገር አልቻሉም፡፡ ቮይስ ኦፍ አሜሪካ (ቪኦኤ) እንደዘገበው፤ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውይይቱ የተካሄደው በተናጠል ነው፡፡ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፋይደን የሁለቱንም ሀገራት ተወካዮች ለሁለት ጊዜያት አነጋግረዋል፡፡ ይህንኑ መረጃ በኤክስ ገጹ ላይ ያረጋገጠው የቱርክዬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም፡፡
ቪኦኤ ሥማቸውን ያልጠቀሳቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሥልጣን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን አሁንም ድረስ እያነጋገረ የሚገኘው ጉዳይ፤ ኢትዮጵያ በፈረንጆች አዲስ ዓመት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት “የሚቀደድበት መንገድ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሶማሊያ የባሕር በር አማራጭ የምታገኝበት መንገድ” የሚገለጽበት ቋንቋ እንዳሉት በዘገባው አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአሸማጋይ በተናጠል ያካሔዱት ውይይት ቀድሞ በተያዘለት ቀጥሮ ሊከናወን የነበረው ከሦስት ሳምንት በኋላ የነበረ ቢሆንም፤ በስምምነት ቀኑ ወደፊት መጥቷል፡፡ የስምምነቱ ቀን ወደት ከመምጣቱ አስቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ጋር በስልክ ተነጋግረዋል፡፡ ኤርዶጋን በተመሣሣይ የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድን በስልክ አነጋግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኤርዶጋን ጋር በስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ጽሕፈት ቤታቸው አረጋግጧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ ውይይት የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያ፤ “በጋራ ስምምነት መንገድ የባሕር በር የማግኘት” አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል ተብሏል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












