ኢትዮጵያ በወደብ ጉዳይ ከሶማሊያ ጋር የምታደርገው ውይይት በቀጣይ ሳምንት በአንካራ እንደሚቀጥል ተነገረ፡፡ ውይይቱ እንደሚቀጥል የተናገሩት የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፋይደን ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ መካከል የሚካሄደው ውይይት እንደሚቀጥል የተናገሩት፤ ከአንድ ሳምንት አስቀድሞ ኢትዮጵያ ደርሰው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ነው፡፡ ፋይደን በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መገናኘታቸውን የሬውስተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ፋይደን በአዲስ አበባ ቆይታቸው በጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር “በዝርዝር ተነጋግረንበታል” ሲሉ በኢስታንቡል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገራቸው በቀጣይ ሳምንት ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን በወደብ ጉዳይ እንደምታደራድር ቢናገሩም፤ ቀኑን ግን በይፋ አልገለጹም፡፡

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቀጣይ ሳምንት በቱርክ አደራዳሪነት የሚያካሄዱት ውይይት ለሁለተኛ ጊዜ የሚከናወን ይሆናል፡፡ ከአንድ ወር በፊት ሰኔ 24፣ 2016 በአንካራ በተደረገ ውይይት የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች ፊት ለፊት ባይነጋገሩም ልዩነቶቻቸውን በሁለቱም ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ ለመፍታት ቅን፣ ልባዊ እና ወደፊት የሚመለከት የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው ተነግሮ ነበር፡፡
በወቅቱ ኢትዮጵያን በመወከል አንካራ ያመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀሥላሴ ናቸው፡፡ ሶማሊያም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን አሕመድ ሙዓሊም ፈቂን ለድርድር ልካለች፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመጀመሪያውን ድርድር በተመለከተ ባወጣው አጭር መግለጫ፤ በውይይቱ “ግልጽ እና ወዳጅነት የተሞላበት የሐሳብ ልውውጥ” ተደርጓል ብሎ ነበር፡፡ የአንካራው ውይይት “በሁለቱ አገራት መካከል ላሉ አለመግባባቶች መፍትሔ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ” እንደነበርም ሚኒስቴሩ በወቅቱ መግለጫው ጠቅሷል።
ተወካዮቹ ባደረጉት ውይይት በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያሉ “አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት” መስማማታቸውን ገልጾ የነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በቀጣይ ሳምንት ይካሄዳል ስለተባለው ውይይት እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












