የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በ2016 የትምህርት ዘመን በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች በቀን እና በማታ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ ተማሪዎች መካከል 94.3 በመቶ የማለፊያ ነጥብ ማስመዝገባቸውን አስታውቋል። ቢሮው የማለፊያ ነጥብ 50 መሆኑን ገልጿል።
የትምህርት ቢሮ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 13/2016 በሰጠው መግለጫ ነው። በዘንድሮው ዓመት ለፈተና የተቀመጡ ተማሪዎች ብዛት 85 ሺሕ 46 መሆኑን በመግለፅ፣ የፈተናውን የማለፊያ ነጥብም ይፋ አድርጓል።
በዚህም የ6ኛ ክፍል ማለፊያ ነጥብ 50 እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉን የአዲስ አበባ ትምህርት ቤት በመግለጫው አመልክቷል። ቢሮው ለአካል ጉዳተኞች የፈተና ማለፊያው ነጥብ 45 እንደሆነም ገልጿል።
የከተማው አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በተመሳሳይ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ማለፊያ ነጥብ ከሳምንት በፊት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይፋ በተደረገው የቢሮው መረጃ የ2016 የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና የማለፊያ ነጥብ ልክ እንደ ስድስተኛ ክፍል ሁሉ 50 ነው። ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ማለፊያ ነጥብ 45 ተደርጓል።












