የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዛሬው እለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካጋጠመው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብልሽት ጋር በተገናኘ መስተጓጎል አለመፈጠሩን አስታወቀ።
አየር መንገዱ ይህን የገለጸው ዛሬ ዐርብ ሐምሌ 12/2016 ከሰዓት ባወጣው አጭር መግለጫ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብልሽት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ባንኮች እና አየር መንገዶች መስተጓጎል እንደገጠማቸው እየገለፁ ይገኛሉ።
በብልሽት ምክንያት የኔትወርክ መቋረጡ ካጋጠማቸው ሀገራት ውስጥ አሜሪካ እና አውስትራሊያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው ከሆነ፤ በአውስትራሊያ ባጋጠመው የኔትወርክ መቆራረጥ ምክንያት ከአየር መንገዶች ውጪ ዝነኛው ስካይ ኒውስ ዩኬ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሙሉ ለሙሉ ሥርጨቱ ቆሞ ነበር፡፡
እንደ ስካይ ኒውስ ዩኬ ሁሉ በአውስትራሊያ አገልግሎት ለማቋረጥ የተገደደው የሀገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ የአውስትራሊያ ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ ለደንበኞቹ አገልግሎት ለመስጠት ተቸግሮ እንደነበር አስታውቋል፡፡
በአውስትራሊያ የተፈጠረውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብልሽት ምክንያት በተመለከተ የአውስትራሊያ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እስካሁን የታወቀ ነገር እንደሌለ በመጥቀስ፤ ጉዳዩ ከዓለም አቀፉ የሳይበር ደኅንነት ተቆጣጣሪ ክራውድ ስትራይክ ጋር የሚገናኝ ነው ብሏል፡፡ የሀገሪቱ የሳይበር ደህንነት ተቆጣጣሪም የኔትወርክ መቆራረጡ ያጋጠመው ጥቃት ተፈጽሞ ነው ለማለት የሚያስችል መረጃ እንዳልተገኘም አያይዞ ገልጿል፡፡
በአንጻሩ የኔትወርክ መቋረጡ የተከሰተው በቴክኒካዊ ችግር ሊሆን እንደሚችልና ከሶፍትዌር ኩባንያው ማይክሮሶፍት ጋር የተገናኘ መላ ምት አስቀምጠዋል፡፡
ከአውስትራሊያ በተጨማሪ የኔትወርክ መቋረጡ በአሜሪካ አላስካ ግዛት ተከስቷል፡፡ የግዛቱ ባለሥልጣናት ኔትወርክ መቋረጡ ሰበብ የአደጋ ጊዜ ጥሪዎች መስተጓጎል ገጥሞናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የዴልታ አየር በኔትወርክ መቆራረጡ በረራዎችን ማራዘሙን ለተጓዦች አሳውቋል።
በአውስትራሊያ እና አሜሪካ ለአንድ ሰዓት ያክል ገጥሟል በተባለው የኔትወርክ መቋረጥ ምክንያት የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እስካሁን ድረስ ይፋ አልተደረገም፡፡
የተጠቃሚዎችን የኢንተርኔት መቆራረጥ የሚከታተለው ዳውን ዲቴክተር የተሰኘ ድረ ገጽ በአማዞን፣ በአሜሪካእና ዴልታ አየር መንገድ የአገልግሎት መቆራረጥ ተመዝግቧል ብሏል።
በዛሬው እለት ያጋጠመው የአይቲ ብልሽት እአአ 2017 ወዲህ ከፍተኛው ነው እየተባለ ነው፡፡
ለችግሩ ምክንያት ሆኖል ተብሎ ሲጠቀስ የነበረው ማይክሮሶፍት የሶፍትዌር ችግሩ መስተካከሉን አስታውቋል፡፡ ችግሩ በሦስተኛው ወገን በተደረገ የሶፍትዌር ማሻሻያ ሙከራ ምክንያት እንደተከሰተ ያስታወቀው ኩባንያው፣ በዚህም ምክንያት ሶፍትዌሮቹ ላይ መጨናነቅ መፈጠሩ ተረጋግጧል ብሏል።












