Homeዜናና ወቅታዊዜናአፋር እና ሶማሌ በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን...

አፋር እና ሶማሌ በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ

የአፋር ክልል እና የሶማሌ ክልል በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስታወቁት በዛሬው እለት ነው፡፡ ክልሎቹ ችግሩን ለመፍታት መስማማታቸውን በርእሰ መስተዳድሮቻቸው በኩል በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ርእሰ መስተዳድሮቹ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 11/2016 በሰጡት መግለጫ በአዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶች እንዳያገረሹና የሰው ሕይወት መጥፋት እንዳይጠፋ ከስምምነት በመድረሳቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ስምምነት ላይ መደረሱ ዘላቂ ሰላም በአዋሳኝ አካባቢዎች እንዲኖር በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል።

ሁለቱ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሳው ግጭት በሕጋዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ እና ሰላማዊ በሆነ አግባብ ብቻ እንዲፈታ ለማድረግ የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን እንደሚመሩት ገልጸዋል፡፡

የአፋር እና ሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድሮች በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ስምምነት ከመድረሳቸው አስቀድሞ ከሦስት ወራት በፊት ሚያዝያ ወር መጀመርያ ላይ በሁለቱ ክልሎች መካከል ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ነበር፡፡


በሁለት ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ለረዥም ጊዜያት እየተፈጠረ ያለውን ‹‹ደም አፋሳሽ ግጭት›› በዘላቂነት ለመፍታት የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረሰው በአዲስ አበባ ከተማ ነበር፡፡ በወቅተ የተደረሰው ስምምነት በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መሪነት የተከናወነ ነው፡፡ የመሪነቱን ኃላፊነት የወሰደው መጅሊስ የካቲት 29/2016 የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች የማኅበረሰብ መሪዎች የተካተቱበት 25 አባላትን ያቀፈ የዕርቀ ሰላም ኮሚቴ በሸራተን አዲስ አቋቁሞ ነበር፡፡


ይህንኑ ተከትሎ ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ መሪዎች ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ ‹‹በአካባቢው የሚካሄደው ግጭት ቆሞ ሁሉም አካል ለውይይትና ለእርቀ ሰላም እንዲቀመጥ››  ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መግለጫው የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተጀመረውን የእርቀ ሰላም ሂደት በሙሉ ልብ እንደተቀበሉት በመግለጽ፣ ለተግባራዊነቱ እንደሚሠሩ አሳውቀው ነበር፡፡

በስምምነቱ ላይ ከመጅሊስ አመራሮች ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት ተወካይ እንዲሁም በአፋር እና በኢሳ በኩል ኡጋዞች እና መሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በአፋር እና በኢሳ መካከል በየጊዜው የሚነሳውን ግጭት ለመፍታት የተቋቋመው የዕርቀ ሰላም ኮሚቴ በመጅሊስ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ የሚመራ ሲሆን፣ ከሶማሌ ክልል በኩል ኡጋዝ መሐመድ ኡጋዝ ጉሬ፣ ኡጋዝ አሊ ቦሩ፣ ሡልጣን አሕመድ ሁሴን፣ ሸይኽ ጣህር ራቢ፣ ሁሴን አብዲ አዳም፣ አሊ ሐሰን ደራር፣ አሰሜ ፋራህ፣ ኢብራሂም አሊ ዋርሰሚ፣ ሡልጣን አብዲ ፋራህ እና በቆሬ ጎለድ ደራር ተካተዋል፡፡


በአንጻሩ ከአፋር ክልል ሸይኽ ሳድቅ ሑሴን ናስር፣ አቶ አቢቶ ሙካ መሐመድ፣ ዶ/ር መሐመድ ሑሴን መሐመድ፣ አቶ አሕመድ ያሲን ሀረል ማሂስ፣ ሸይኽ ሰኢድ አብዱልቃድር፣ አቶ ኢብራሂም ቢልአይቱ፣ ሸይኽ አሊስ ሁመድ፣ አቶ ሴኮ መሐመድ ሰዒድ፣ ሸይኽ አወል መሐመድ ድምስ እና ሸይኽ ጀውሃር መሐመድ የኮሚቴው አባላት ናቸው፡፡ ኮሚቴው ከገለልተኛ አካላት የመጅሊሱን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፣ ሐጂ አባቢያ አባጨብሳ፣ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እና ሐጂ ከማል ዓብዱልቃድርን ያቀፈ ነው፡፡

ከዛሬው ስምምነት በኋላ የተናገሩት ከገለልተኛ አካላት የተወከሉት ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ ስምምነቱ ወደ መሬት ወርዶ የሚፈለገውን ውጤት ያመጣ ዘንድ ሁሉም ባለ ድርሻ አካል የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular