Homeዜናና ወቅታዊዜናየአምስተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ተጀምሯል ተባለ

የአምስተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ተጀምሯል ተባለ

የአምስተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መጀመሩን የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ይፋዊ ማረጋገጫ ያልተሰጠበት የግድቡ የውሃ ሙሌት፤ በቀጣይ ሳምንታት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

የግብጽ መገናኛ ብዙኃን አምስተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ተጀምሯል ያሉት የሀገሪቱ ጂኦሎጆስቶች ያያዙትን ምስል ዋቢ አድርገው ነው፡፡

የግብጽ መገናኛ ብዙኃን እና ባለሞያዎች ኢትዮጵያ አምስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ጀምራለች የሚለው መረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ አራተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ስታከናውን “የመጨረሻው” እንደሚሆን ከተናገሩት ጋር የሚጣረስ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ ዓመት ዋዜማ የሕዳሴ ግድብ አራተኛ እና የመጨረሻ ዙር ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን የተናገሩት የግድቡ ግንባታ በሚገኝበት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ተገኝተው ነበር፡፡

ዐቢይ በወቅቱ የተከናወነውን አራተኛውን ዙር ሙሌት “የመጨረሻው” ነው ቢሉም የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ ስለጉዳዩ በመገናኛ ብዙኃን ማረጋገጫ እንዲሰጡ ተጠይቀው ማብራሪያ ለመስጠት ፍቃደኛ እንዳልሆኑ በመግለጽ፤ መገናኛ ብዙኃኑን ስለ ጉዳዩ “መንግሥት ባለው መሠረት ብትጠቀሙ የተሻለ ነው” የሚል መልስ ሰጥተው አልፈውታል፡፡

አራተኛውን ዙር ሙሌት የመጨረሻ ባለው በመንግሥት በኩል፤ አምስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጀመሩን በተመለከተ እስካሁን ድረስ የተሰጠ ማብራሪያ የለም፡፡

ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት መጀመሪያ በክረምቱ ተጨማሪ የውኃ ድጋፍ አራተኛው ዙር በስኬት መጠናቀቁን ኢትዮጵያ ይፋ ስታበስር፤ ግብፅ በተደጋጋሚ እንደምታደርገው ተቃውሞዋን አሰምታ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የግብፅን የተቃውሞ መግለጫ መሠረተ ቢስና የተለመደ “የሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

ከ13 ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ያስጀመረችው፤ በጨለማ ውስጥ ያለው 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን እንዲያገኝ መሆኑን በተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ መድረኮች ትገልጻለች፡፡ ሆኖም ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ አሁን እስከደረሰበት መገባደጃው ድረስ በሱዳን እና ግብጽ ተቃውሞ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular