የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚካሄደው አጀንዳ ማሰብሳብ በቀጣይ ሳምንት አጋማሽ እንደሚጀመር ያስታወቀው በዛሬው እለት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 10/2016 በዋና መሥሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ በክልሎች የሚያደርገውን የአጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በቀጣዩ ሳምንት በይፋ ይጀመራል ብሏል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ በሰጡት መግለጫ፤ የምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት የሚከናወንባቸር ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ናቸው። ይህንኑ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ ሒደት ቤንሻንጉልን ጨምሮ በቀጣይነት ለማካሄድ የተወሰነው አጀንዳ በማሰባሰብ የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣ አስቀድሞ ስለተጠናቀቀባቸው መሆኑም ተነግሯል፡፡ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኃላፊዎች በክልሎቹ የሚጀመረው አጀንዳ ማሰባሰብ በተያዘው ሳምንት እንደሚጀመር ቀደም ብለው አሳውቀው የነበረ ቢሆንም ዛሬ በሰጡት መግለጫ የቀን ለውጥ ተደርጓል።
በሦስት ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ የሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፤ በስድስት ቀን ለመጨረስ መታቀዱ ሲገለጽ፤ ለዚሁ ሒደት ይረዳ ዘንድ የኮሚሽኑን ባለሞያዎችን የያዘ ቡድን ሐምሌ 9/2016 ወደ አሶሳ ከተማ መጓዙን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡
በየክልሎቹ የሚኖረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቀጣይ ረቡዕ ይጀምራል የተባለ ሲሆን፣ የቀሪዎቹ ክልሎችና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሂደት ከሌሎች ማህበራዊ ክንውኖች ጋር በተገናኘ ጥቂት መዘግየት ሊኖረው እንደሚችል ሚንበር ቲቪ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኃላፊዎች ሰምቷል፡፡ በክልሎች እና በድሬዳዋ የሚኖረው የአጀንዳ ማሰብሳብ ሒደት ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ከተካሄደው ጋር ተመሳሳይ ይሆናል ተብሏል፡፡
በዛሬው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጫ ወቅት አጀንዳ ማሳባሰቡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ዜጎች ውጪ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትየጵያውያንን የሚያሳትፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ ማስያዝ ከፈለጉ ኮሚሽኑ በሚያስቀምጠው አድራሻ መላክ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ውይይት ለማካሄድ በሒደት ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታኅሣሥ 2014 በጸደቀ የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ በመንግሥት እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮችን እንደሚለይ አሥፍሯል።












