ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ዋጋቸው እኩል የሆኑ ምርቶችን መለዋወጥ የሚያስችለውን የገንዘብ ልውውጥ ስምምነት በባንክ ገዥዎቻቸው በኩል ተፈራረሙ፡፡ የገንዘብ ልውውጥ ስምምነቱ ዋጋቸው እኩል የሆኑ ምርቶችን መለዋወጥ የሚያስችል እንዲሁም ከምርቶቹ ዋጋ በላይ የሆነውን ትርፍ ዋጋ ብቻ በገንዘብ የሚያወራርድ ነው ተብሏል፡፡
ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 9/2016 የተደረሰው ስምምነት፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ እና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኻሊድ ሙሐመድ ተፈርሟል፡፡
አዲስ የተፈረመው የ817 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው ስምምነት ሁለቱ ሀገሮች እስከ 46 ቢሊዮን ብር ለመለዋወጥ ያስችላቸዋል። የኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የገንዘብ ስምምነት ዓላማ የሁለትዮሽ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የፋይናንስ ትብብሮችን ማጠናከር ነው የተባለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ አማራጭ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዲኖራት እንደሚስችላትም ተጠቁሟል፡፡
ዋጋቸው እኩል የሆኑ ምርቶችን መለዋወጥ በሚያስችለው በዚህ ስምምነት፤ ከምርቶቹ ዋጋ በላይ የሆነ ትርፍ ዋጋ በገንዘብ የሚወራረድበት ነው፡፡ የገንዘብ ልውውጥ ስምምነት ኢትዮጵያን ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች በብር መግዛት ያስችላታል፡፡ በአንጻሩ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችም በድርሐም ከኢትዮጵያ መግዛት የምትችል ይሆናል፡፡
በተለይ በብሪክስ ሀገሮች በሥፋት የሚተገበረው የገንዘብ ልውውጥ ስምምነት፤ ሀገሮች ከአሜሪካ ዶላር ተጽዕኖ ለመላቀቅ የሚያደርጉት መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ከሀገሮቹ መካከል በተለይ ቻይና ከዶላር ለመላቀቅ ባለፉት ወራት የታዳጊ ሀገሮች መንግሥታትን ለማስተባበር ስትንቀሳቀስ ነበር፡፡ ሀገሪቱ የገንዘብ ልውውጥ ስምምነት ለማድረግ በዕቅድ የያዘችው በ29 ታዳጊ ሀገሮች ነው፡፡
ከቻይና በተጨማሪ ሌሎቹ የብሪክስ ሀገሮች ሩሲያ እና ሕንድ በብሪክስ ሥር ተመሳሳይ ስምምነት አድርገው በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ጋር የገንዘብ ልውውጥ ስምምነት የተፈራረመችው ኢትዮጵያ፤ እንደ ስምምነት ተጋሪዋ ኤምሬቶች ሁሉ ብሪክስን የተቀላቀለችው በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የመጀመርያ ቀን ነው፡፡ ብሪክስ የተመሠረተው እ.አ.አ በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና ሲሆን፣ አምስተኛዋ ሀገር ደቡብ አፍሪካ ስብስቡን የተቀላቀለችው በ2010 ነበር፡፡
ስብስቡ የሰሜን አሜሪካ እና የምዕራብ አውሮፓ የበለጸጉ አገራትን ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ኃይል ለመቋቋም እና ለመገዳደር በዓለም ላይ በጣም ወሳኝ የሚባሉ በመልማት ላይ ያሉ ሀገሮችን አንድ ላይ ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑን ይገልጻል፡፡












