ፈረንሳይ በተያዘው ሐምሌ ወር መገባደጃ በምታዘጋጀው ኦሎምፒክ የምታሳትፋቸው ሙስሊም አትሌቶች ሒጃብ እንዳይለብሱ መከልክሏ ተቃውሞ አስከተለባት። ሀገሪቱን የተቃወመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ነው፡፡
የመብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኦሎምፒክ ውድድሮችን አዘጋጇ ፈረንሳይ አትሌቶቿ ሒጃብ እንዳያደርጉ መከልከሏን የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው ብሎታል። አምነስቲ ከፈረንሳይ በተጨማሪ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ላይ ትችት ሰንዝሯል፡፡ ተቋሙ የኦሎምፒክ ኮሚቴውን የተቸው አግላይ ሲል የጠራውን የፈረንሳይ ውሳኔ በመቀበሉ ነው፡፡
በኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ሙስሊም አትሌቶቿን ሒጃብ አድርገው ከመወዳደር የከለከለችው ፈረንሳይ፤ ስፖርተኞቿ ሀገር ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ሒጃብ አድርገው እንዳይታዩ እቀባ ጥላለች፡፡ ሀገሪቱ ይህን አቋም የምታራምደው፤ እከተለዋለሁ በምትለው የሴኩላሪዝም ፖሊሲ ነው፡፡
ሴኩላሪዝም ነው የምትከተለው የምትለው ፈረንሳይ ሙስሊሞችን በተለየ ሁኔታ በመጨቆን በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብባት ነች፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በፈረንሳይ ላይ ቅሬታ የሚያቀርቡት የራሷ ዜጎች ጭምር ናቸው፡፡
በኦሎምፒክ ውድድር ላይ አትሌቶቼ ሒጃብ አድርገው መወዳደር አይችሉም ያለችው ፈረንሳይ፤ በውድድሩ ላይ የሒጃብ ክልከላ የጣለች ብቸኛዋ አውሮፓዊት ሀገር ሆናለች፡፡ ፈረንሳይ የጣለችው የሒጃብ ክልከላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስፖርታዊ ውድድሮችን የሚያስተዳድሩት እንደ እግር ኳስ አለቃው ፊፋ፣ የዓለም አቀፉ የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የመረብ ኳስ ፌዴሬሽን ሕግጋት ጋር የሚቃረን ነው፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ፤ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ባለፉት ዓመታት የሴኩላሪዝምን ጽንሰ ሐሳብ ሙስሊም ሴቶችን ለመጨቆን እያዋሉት ነው ሲል ተችቷል፡፡ እንደ አምነስቲ ሁሉ ውሳኔውን ከተቹ የመብት ተቋማት መካከል የሆነው ሒጃብ እንዲለበስ የሚሟገተው ሌ ሂጃቢስ፣ የሀገሪቱን ውሳኔ እስከመጨረሻው እንደሚፋለመው አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ ፈረንሳይም ሆነ ዓለም አቀፉ የአሎምፒክ ኮሚቴ ውሳኔውን ለመቀልበስ እንዳልረፈደባቸው ጠቁሟል።
ፈረንሳይ ከአጠቃላይ ነዋሪዎቿ ውስጥ 9 በመቶ ሙስሊም ነዋሪዎችን ይዛለች፡፡ ሆኖም በ2019 በወጣ ሪፖርት ከጠቅላላ ሙስሊም ማኅበረሰቡ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት ‘በሃማኖታችን ምክንያት መገለል ይደርስብናል’ የሚል እምነት አላቸው፡፡ በዚህ መገለል ሳቢያ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ማነሱን እንዲሁም በበቂ መጠን ውክልና ማግኘት አልቻልንም የሚሉ ናቸው፡፡
ሀገሪቱ ከ2021 ጀምሮ በአደባባይ ኒቃብ እንዳይለበስ መከልከሏም በሥፋት ተቃውሞ የተሰማበት ነበር፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ሒጃብ እና አባያን በትምህርት ቤቶች ለመከልከል ሲወተውቱ መታየታቸውም አዲስ አይደለም፡፡












