የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተያዘው ሣምንት አንስቶ ድሬዳዋ እና ሐረርን ጨምሮ በአራት አካባቢዎች የአጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡ የአጀንዳ ማሰባሰቡ እስከ ነሐሴ መጨረሻ ይቀጥላል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተያዘው ሳምንት አጀንዳ የማሰባሰብና የማወያየት ሥራ ይጀመርባቸዋል ያላቸው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሦስት ክልሎች ናቸው፡፡ የኮሚሽኑ ዋና ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሥፍን አርዓያ የማሰባሰብና የማወያየት ሥራ የሚጀመርባቸው በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ በሐረር፣ በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሮች ምደባ በማካሄድ በአንድ ጊዜ ወደ አራት ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው እንደሚሠራ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ የክረምቱ ሁኔታ ካላስቸገረ እስከ ነሐሴ 30/ 2016 ድረስ በአብዛኛው ክልሎች አጀንዳ የማሰብሰብ ሥራው እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ምክክር ኮሚሽኑ በአፋር ክልል በዚህ ወቅት ሙቀቱ እየበረታ የሚሄድበት መሆኑን በመግለጽ፤ ሙቀቱ እየቀነሰ ሲመጣ በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን ለማስጀመር መታሰቡን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የመጀመሪያውን አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማካሄዱ ይታወሳል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት አንዳንድ ክፍተቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፤ ከተማዋ ሠፊ እንደመሆኗ የነበረውም ጊዜ አጭር ስለነበር ለተሳታፊ ጥሪ በሚደረግበት ወቅት ክፍተቶች መፈጠራቸውን ታዝበናል ሲሉ አንስተዋል።

በዚህም የሃይማኖት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ወደ ምክክሩ በማምጣት ሂደትና ታዋቂ ሰዎችን ወደ ስብሰባው በማቅረብ ሂደት ላይ በተወሰነ ደረጃ ክፍተቶች ነበሩ ያሉት ፕሮፌሰር መሥፍን፤ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ማኅበረሰቡ እንዲረዳና በቀጣይ ለማስተካከል ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በተጨማሪ በሱማሌ ክልል የተሳታፊ ልየታና መረጣ በሚደረግበት ወቅት በሁለት ዞኖች ላይ ባጋጠመው የጤና ችግር ምክንያት ችግር መፈጠሩን ጠቁመው፤ አሁን ላይ አንድ ኮሚሽነር እና ባለሞያዎች ተልከው የተሳታፊ ልየታ እያደረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያካሄደ በሚገኘው የምክክር ሂደት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንዲሁም የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ምክር ቤቶች ከውክልና ጋር ተያይዞ ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር በአሁኑ ወቅት የሂደቱ ተሳታፊዎች ልየታና መረጣ በ10 ክልሎች መጠናቀቁን የገለጹ ሲሆን፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ላይ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን አመልክተ ዋል።
በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ውይይት ለማካሄድ በሒደት ላይ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታኅሣሥ 2014 በጸደቀ የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ በመንግሥት እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮችን እንደሚለይ አሥፍሯል።
ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡለትን እነዚህን አጀንዳዎች ካደራጀ በኋላ ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የመለየት ሚና በአዋጁ ተሰጥቶታል። ተወካይ ያስመርጣሉ ተብለው ከተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን እና የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የተገለሉ ኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ዕድሮች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተካተዋል።












