ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ካቀኑ ኢትዮጵያዊያን መካከል የመጨረሻዎቹ በነገው እለት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) አስታወቀ። ነገ እሑድ አዲስ አበባ የሚገቡት ሑጃጅ ቁጥር 107 መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል።
በጠቅላይ ምክር ቤቱ የሐጅና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዓብዱልፈታህ ሙሐመድ ናስር፣ ሥርዓታቸውን ፈጽመው ያጠናቀቁ የመጨረሻዎቹ ኢትዮጵያዊያን እሑድ ሐምሌ 7/2016 ንጋት ላይ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።
በዘንድሮው ዓመት በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኩል ለሐጅ ክንውን 12 ሺሕ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ማቅናታቸው ይታወቃል። ከተጓዦች መካከል የሐጅ ሥርዓታቸውን ፈጽመው ያጠናቀቁ ከሰኔ 16፣ 2016 ጀምሮ ወደ ሀገር ቤት እየተመለሱ ይገኛሉ።
የመጨረሻዎቹ 107 ሐጃጆች ሌሊቱን ከጅዳ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው ንጋት ላይ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይደርሳሉ ተብሎ ተጠብቋል።
በ1445 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዓት ላይ ከመላው ዓለም ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን መሳተፋቸውን የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።












