Homeዜናና ወቅታዊዜናኢትዮጵያውያን ሑጃጅ ወደ ኢትዮጵያ ተጠቃለው የሚገቡበት ቀን ታወቀ

ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ ወደ ኢትዮጵያ ተጠቃለው የሚገቡበት ቀን ታወቀ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ለሐጅ ክንውን ሳዑዲ ዐረቢያ ያቀኑ ኢትዮጵያውያን ተጠቃለው ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበትን ቀን አስታወቀ፡፡ በሐጅ ክንውን ከተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ ሳዑዲ ዐረቢያ የቀሩት 1 ሺሕ 119 ብቻ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ሚንበር ቲቪ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንደሰማው፣ የሐጅ ክንውኑ መጠናቀቁን ተከትሎ ምዕመናኑ በሔዱበት ቅደም ተከተል መሠረት እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ ምክር ቤቱ እሑድ ሐምሌ 7/2016 ንጋት ድረስ የቀሩት 1 ሺ 119 ሑጃጅ ሀገር ቤት እንደሚመለሱ ገልጧል፡፡

በዘንድሮው ዓመት በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮ ጠቅላይ ምክር ቤቱ በኩል ለሐጅ ክንውን ወደ መካ የተጓዙ ኢትዮጵያዊያን ምዕመናን ቁጥር 12 ሺህ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

ከአስር ቀናት በፊት በወጣ መረጃ፤ ለሐጅ ክንውን ወደ ሳዑዲ ካመሩ ኢትዮጵያውያን ውስጥ የአስር ኢትዮጵያውያን ሕይወት ሲያልፍ፣ ቀሪዎቹ ክንውኑን በሠላም አጠናቀዋል ተብሏል፡፡ አስሩ ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ በሙሉ በመካ ከተማ መስጂደል ሐረም ሶላተል ጀናዛ ተሰግዶባቸው የቀብር ሥርዓታቸው ተፈጽሟል ተብሏል። ሕይወታቸው ካለፈው መካከል የአምስቱ ሐጃጅ ሕይወት የሐጅ ሥነ ሥርዓት ከመጀመሩ በፊት ማለፉ ሲገለፅ፣ የሌሎቹ ሕይወት ያለፈው በዓረፋ ወቅት ነው።

የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው አሐዝ መሠረት፤ በዘንድሮው ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ከመላው ዓለም 1 ሚሊዮን 833 ሺሕ 164 ምዕመናን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በሐጅ ክንውን ላይ ከተሳተፉት መካከል 1 ሚሊዮን 611 ሺሕ 310 ምዕመናን ከሳዑዲ ዐረቢያ ውጪ ካሉ ሀገራት መካ ከተማ የገቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 221 ሺሕ 854 ነዋሪነታቸው በዚያው በሳዑዲ ዐረቢያ ነው፡፡ በሐጅ ሥነ ሥርዐቱ ላይ 52.27 በመቶውን ቁጥር ያስመዘገቡት ወንዶች ናቸው፡፡ የሴት ምዕመናን ቁጥር 47.73 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በክንውኑ ላይ ከተሳተፉት መካከል 1 ሚሊዮን 546 ሺሕ 345 ምዕመናን ሳዑዲ ዐረቢያ የደረሱት በአውሮፕላን ተሳፍረው ነው የተባለ ሲሆን፣ 60 ሺሕ 251 ምዕመናን በየብስ እንዲሁም 4 ሺሕ 714 ምዕመናን ደግሞ በባሕር አቋርጠው መካ ደርሰው የሐጅ ሥርዐቱን ፈጽመዋል፡፡

ከሑጃጅ መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከእስያ አሕጉር የተነሱት መሆናቸውን ያመለከተው የሳዑዲ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር፣ 22.3 በመቶዎቹ ከዐረብ ሀገራት፣ ከአፍሪካ 11.3 በመቶ፤ ከአውሮፓ፣ ሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም አውስትራሊያ የተነሱት 3.2 በመቶ መሆናቸውን ገልጧል፡፡

(በዚህ ዜና ላይ ከቆይታ በኋላ መጠነኛ የመረጃ ማስተካከያ ተደርጎበታል)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular