Home ዜናና ወቅታዊ ዜና የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ ውል ምዝገባ ቀን ተራዘመ

የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ ውል ምዝገባ ቀን ተራዘመ


የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ፤ በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት አከራይና ተከራይ ውል የሚፈጽሙበትን ቀን ማራዘሙን አስታወቀ፡፡ የምዝገባ ጊዜው እስከ ሐምሌ መገባደጃ ቀናት ይቀጥላል ተብሏል፡፡  

ቢሮው ከዚህ ቀደም ባወጣው የጊዜ ሠሌዳ የውል ምዝገባ ቀኑ ሰኔ 30/ 2016 መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ ሆኖም ከተመዝጋቢ ብዛት አንፃር በተጠቀሰው ቀነ ገደብ ውስጥ ምዝገባውን “ለማጠናቀቅ አስቸጋሪ ስለሚሆን” ከተመዝጋቢዎች በተነሳ ጥያቄ ቀኑን ለማራዘም ተገድጃለሁ ብሏል፡፡

በአዲሱ የጊዜ ሠሌዳ የአከራይ እና ተከራይ ውል እስከ ሐምሌ 24/ 2016  ተራዝሟል፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ አከራይ እና ተከራይ  ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጭ፣ ቅዳሜ እና እሑድን ጨምሮ ውል እንዲፈጽሙ አሳስቧል፡፡

የመኖሪያ ቤት አከራይ እና ተከራይ ውል ለሁለት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ ውሉ በሚፈጸምበት በዚህ ወቅት የመኖሪያ ቤት አከራዮች ተከራይ ማስወጣትም ሆነ የቤት ኪራይ መጨመር አይችሉም ተብሏል።

የመኖሪያ ቤት አከራይ እና ተከራይ ውል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24/2016 ያፀደቀውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅን መሠረት በማድረግ የሚፈጸም ነው፡፡ በአዲሱ አዋጅ ያልተረጋገጠና ያልተመዘገበ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል እንዳልተደረገ ይቆጠራል፡፡ ውል ያልፈጸሙ አከራይም ሆነ ተከራይ ባልተመዘገበ የኪራይ ውል መብታቸውን ሊጠይቁ አይችሉም ተብሏል፡፡ የኪራይ ውሉን የማረጋገጥና የማስመዝገብ ግዴታቸውን ያልተወጡ አከራይና ተከራይ ላይ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣል አዋጁ ይደነግጋል። የገንዘብ ቅጣት መጠኑ የተቆጣጣሪው አካል በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን ሲሆን፣ ቅጣቱ ከሦስት ወር የቤቱ ኪራይ እንደማይበልጥ አዋጁ ገደብ አስቀምጧል።

አዋጁ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካል በሚወስነው መሠረት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንዲተገበር ያደርጋል፡፡

አዋጁ የቤት ኪራይ የክፍያ ሥርዓት “በባንክ ወይም በሌላ ሕጋዊ በሆነ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ ብቻ” እንዲፈጸም የሚያስገድድ ነው። (ሚንበር ቲቪ)

NO COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here