ሰኞ , محرم 9, 1446
Google search engine
Homeዜናና ወቅታዊዜናለሦስተኛ ጊዜ ማሻሻያ የተደረገበት የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ፀደቀ

ለሦስተኛ ጊዜ ማሻሻያ የተደረገበት የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ፀደቀ


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሦስተኛ ጊዜ ማሻሻያ የተደረገበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ አፀደቀ፡፡ ምክር ቤቱ አዋጁን ያጸደቀው ያለ ተቃውሞ በሙሉ ድምጽ ነው፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 27/ 2016 ባካሔደው 36ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ያጸደቀው አዋጅ፤ ከሁለት አስርት ዓመት በፊት ፀድቆ ለሁለት ጊዜ ማሻሻያ የተደረገበት ነው፡፡ የተሻሻለው አዋጅ ላይ የቤተ እምነቶች፣ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንዲሁም የኤሌክትሪክ እና የውሀ ፍጆታ የተመለከቱ አንቀፆች ተካተውበታል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ አዋጅ፣ ቤተ እምነቶችን ከታክስ ሙሉ ለሙሉ ነፃ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡ አዋጁ ቤተ እምነቶች ከታክስ ነፃ የማይደረጉባቸውን አማራጮች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

በአዋጁ የሃይማኖት ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ ከግሉ ንግድ ዘርፍ ጋር ተወዳዳሪ ሆነው በሚሠሯቸው በሆቴል ንግድ ሥራ ዘርፍ እና ሕንጻ አከራይተው ገቢ በሚያገኙባቸው ሥራዎች ላይ ተገቢውን ግብርና ታክስ መክፈል እንደሚገባቸው ደንግጓል፡፡

በጉዳዩ ላይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የምትሰበስበው ታክስ ለጠቅላላ ምርቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ በመሆኑ መንግሥት በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመታት ይህን ለማስተካከል እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ኢዮብ (ዶ/ር) ይህን ለማሳካት የታክስ ፖሊሲዎችን ማስተካከል፣ አዳዲስ የታክስ ፖሊሲዎችን መቅረፅ እንዲሁም የታክስ አስተዳደሩን ማዘመን እንደሚገባና ለዚህም ረቂቅ አዋጁ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ከተጨማሪ እሴት ታክስ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ደረጃዎች እና የሕጋዊ ስነ-ልክ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡ አዋጁ ልኬትን፣ የልኬት አሀድ ሥርዓትን፣ የመለኪያ መሣሪያዎችን እና የታሸጉ ምርቶችን በመቆጣጠር ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት በማስፈን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ ነው ተብሏል፡፡


RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Google search engine

Most Popular

Recent Comments