በዓለማችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘግቡ ከሚገኙ ሀገሮች መካከል በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ቻይና፤ የሐላል ኢንዱስትሪን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላት ገለጸች፡፡ ሀገሪቱ በዘርፉ ከማሌዥያ ጋር የመሥራት ፍላጎት አላት ተብሏል፡፡
የቻይና ፍላጎት ይፋ የተደረገው፤ በማሌዥያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ነው፡፡ የማሌዥያ ባለሥልጣናት በሐላል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቻይና ከሀገሪቱ ጋር ለመሥራት ፍላጎት አሳይታለች ብለዋል፡፡ የማሌዥያ ባለሥልጣናት በቻይና ባደረጉት ገብኝት ስለ ሐላል ኢንዱስትሪ ማብራሪያ መስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የማሌዥያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቱክ ሙሐመድ አላሚን እንደተናገሩት፣ ቻይና በሐላል ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሐላል ምዘና ሰርተፍኬት አሰጣጥ፣ አገልግሎት እንዲሁም በሐላል ምርቶች አቅርቦት ላይ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት አሳይታለች፡፡
ቻይና በሐላል ኢንዱስትሪ ላይ ለመሥራት ፍላጎቷን የገለጸችው፣ የማሌዥያ ባለሥልጣናት ወደ ቻይና ለጉብኝት አምርተው በነበረበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚሁ ጉብኝት ወቅት ከቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር ቆይታ የነበራቸው የማሌዥያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቱክ ሙሐመድ አላሚን፤ ስለ ሐላል ኢንዱስትሪ ገለጻ አድርገዋል ተብሏል፡፡
ቻይና ከማሌዥያ ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት ያሳየችበት የሐላል ኢንዱስትሪ፣ እ.አ.አ በ2018 3.1 ትሪሊዮን ዶላር ግምት የነበረው ሲሆን፣ በየዓመቱ የ4.1 በመቶ ዕድገት የሚያስመዘግብ ነው፡፡ የሐላል አንዱስትሪ ከስድስት ዓመት በኋላ የሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ በ2030 አምስት ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡
የሐላል ኢንዱስትሪ ሰባት ዘርፎችን በሥሩ የሚያቅፍ ነው፡፡ ይህ ኢንዱስትሪ፤ በሥሩ ሐላል ምግብን ጨምሮ እስላማዊ ፋይናንስ፣ ሐላል ቱሪዝም፣ ሐላል ፋሽን፣ ሐላል ሚዲያ እና መዝናኛ፣ የመድኃኒት እና ሐላል መዋቢያዎችን የሚያካትት ነው።
በሐላል ኢንዱስትሪ በተለይ በኤክስፖርት ዘርፍ ቀዳሚቹን ደረጃዎች የያዙት ሙስሊሞች በቁጥር አነስተኛ የሆኑባቸው የዓለም በሀገራት ናቸው፡፡ በኤክስፖርት የመጀመሪያዎቹን ሦስት ረድፎች የያዙት ሕንድ፣ ብራዚል እና አሜሪካ ናቸው፡፡
አሁን ዘርፉን ለመቀላቀል ፍላጎት ያሳየችው ቻይና፣ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ አላት፡፡ በቻይና የመስሊሞች ቁጥር ከሁለት በመቶ በታች ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












